ኢትዮጵያ ረሃብን በመዋጋት ተሞክሮ የሚሆን ውጤት አስመዝግባለች

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት ረሃብን በመዋጋት ረገድ ተሞክሮ የሚወሰድበት ውጤት ማስመዝገቧን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትናንትና መካሄድ በጀመረው ‹‹ከረሃብ ነፃ ዓለም መፍጠር›› በተሰኘው ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በድህነት ቅነሳና የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ ሥራዋ የላቁ ተግባራትን እየፈጸመች ትገኛለች፡፡

በተለይ በስንዴ ልማት ሥራዎች ለሌሎች ተሞክሮ ሊሰጡ የሚችሉ የግብርና ሥራዎችን ዘመናዊ በሆነ መንገድ እየከወነች መሆኑን ተናግረዋል።

የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረትና የግብርና ግብዓት አቅርቦት እጥረት ፈተና መሆኑን ጠቁመው፤ ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በግብርና ማሻሻያ ላይ ትኩረት ሰጥታ መሥራቷንና ድርቅን መቋቋም የሚችሉ ሰብሎችን በመዝራት ምርታማነት ማሳደጓን ጠቁመዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ዓለምን የተፈታተኑ ታላላቅ ችግሮች ቢኖሩም ጥረትን በእጥፍ በመጨመርና ፈጠራ የታከለባቸውን ሥራዎች በመተግበር ፈተናዎችን መቋቋም ተችሏል። ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት በግብርና ምርታማነት ላይ ስትራቴጂካዊ ለውጥ በማምጣት ሰፋፊ ድሎችን ማስመዝገብ ችላለች።

በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ ከመጣው የሕዝብ ቁጥር አንጻር የምግብ ፍላጎት በእጅጉን ማደጉን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህን ፍላጎት ለመመለስም ምርታማነትን ከማሻሻል በላይ በግብርና ዘርፍ ላይ የሚታዩ መዋቅራዊ ችግሮች መፍታት ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚታረስ መሬትን በእጥፍ በመጨመር ምርታማነትን ማሻሻል መቻሉንም ጠቅሰው፤ በስንዴ፣ በጤፍ፣ በቆሎና ገብስ ምርቶች ላይ ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን አንስተዋል።

በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት 230 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በማምረት የሀገር ውስጥ ፍጆታን በመሸፈን ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል። በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አማካኝነትም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባት መቻሉን ገልጸዋል።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ካደረገችባቸው ዘርፎች መካከል የግብርናው ዘርፍ ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁመው፣ እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን ለመቻል በግብርናው ዘርፍ ባከናወነችው ዘርፈ ብዙ ተግባራት በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) መሸለሟንም አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ ባለፉት ዓመታት ግብርናን ከኢንዱስትሪ ጋር በማስተሳሰር ትልቅ ለውጥ ማምጣቷን የገለጹት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ማስፋፋት፣ የግል ዘርፉን በማበረታታት ኢትዮጵያ በዘርፉ ውጤታማ ለውጥ እንድታመጣና ዓለም አቀፍ እውቅናን እንድታገኝ ያስቻሏት ጥረቶች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(ዩኒዶ)፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የኢትዮጵያ መንግሥትና የዓለም የምግብ ድርጅት (ፋኦ) በጋራ ያዘጋጁት ከረሃብ ነፃ ዓለም ጉባኤ ከትናንትና ጀምሮ ለቀጣይ ሦስት ቀናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል። በጉባኤው ከአንድ ሺህ 500 በላይ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው። በዋናነት ዓለማችን የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ ችግርን ከመሠረቱ ሊፈቱ የሚችሉ የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የሚመክር ጉባኤ መሆኑን ተገልጿል።

በሞገስ ፀጋዬ እና በአዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን  ጥቅት 27/207 ዓ.ም

Recommended For You