አዲስ አበባ፡– በኢትዮጵያ በዓመት ሰባት ሺህ ሰዎች በኤች አይ ቪ ቫይረስ እንደሚያዙ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ በቫይረሱ ምክንያት በዓመት ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚሞቱ ተገልጿል፡፡
ትኩረቱን በፀረ-ኤች አይ ቪ መድኃኒት ተጠቃሚዎች አገልግሎት ላይ ያደረገ የማኅበረሰብ መር ክትትል ፕሮጀክት ትናንትና ይፋ ሆኗል።
በጤና ሚኒስቴር የኤች አይ ቪ፣ ሄፒታይተስና አባላዘር በሽታ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ያደታ በመርሐ-ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ በዓመት ከሰባት ሺህ በላይ አዲስ ሰዎች በቫይረሱ የሚያዙ ሲሆን፤ ከ10 ሺህ በላይ ዜጎች በየዓመቱ ይሞታሉ።
በመላ ሀገሪቷ የሚገኙ 605 ሺህ ሰዎች የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ይገኛል ተብሎ ይገመታል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ ሥርጭቱ እየቀነሰ መምጣቱን ጠቅሰው፤ አዲስ የሚያዙ ሰዎች እድሜያቸው በአማካኝ ከ15 እስከ 29 መካከል እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የበሽታው ምጣኔ በአዲስ አበባ፣ በጋምቤላ እና በትላልቅ ከተሞች ከፍ ያለ መሆኑን አንስተው፤ እንደአጠቃላይ ምጣኔው ከሀገሪቱ ሕዝብ ከአንድ በመቶ በታች ቢሆንም ሥርጭቱ ቀላል የሚባል ባለመሆኑ ግንዛቤው ላይ ሊሠራ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
ቫይረሱን ለመከላከል የኮንዶም ስርጭት ወሳኝ መሆኑን የገለጹት አቶ ፍቃዱ፤ ኮንዶም የመግዛትና የማሰራጨት አቅም ውስን በመሆኑ በተለይ ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑና ትኩረት ለሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገዝቶ እየተሰራጨ መሆኑን ተናግረዋል።
ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭና ትኩረት ለሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች በመንግሥትና በአጋር ድርጅቶች እንደሚገዛ ጠቅሰው፤ ዲኬቲ ኢትዮጵያን ጨምሮ በግል ነጋዴዎች በኩልም ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ከታክስ ነፃ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ኤች አይ ቪ ኤድስን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንጻር የቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎች የሚሰጣቸውን አገልግሎት ለማጠናከር የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የጣምራ ለማኅበራዊ ልማት ድርጅት ዳይሬክተር አቶ ብሩክ ይርጋለም በበኩላቸው፤ የፕሮጀክቱ ዓላማ በማኅበረሰብ መር ክትትል የአገልግሎት አሰጣጥን ማሳደግ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት ተጠቃሚዎች ፍላጎት ላይ ያተኮረ ነው ያሉት ዳሬክተሩ፤ 14 ድርጅቶች በጋራ ሆነው በ12 ክልሎችና ሁለት ከተሞች፣ በ84 ወረዳዎችና 103 ጤና ተቋማት ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።
ከ47 ሺህ በላይ የፀረ-ኤችአይቪ መድኃኒት ተጠቃሚ ቤተሰቦቻችን የአገልግሎት ፍላጎት ተደራሽ ለማድረግ የሚረዳ ፕሮጀክት መሆኑን አስረድተዋል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ጥቅት 27/207 ዓ.ም