“አሕጉራዊው ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነቱ አጀንዳ 2063ን ተግባራዊ ለማድረግ ያግዛል” ያስሚን ወሃረቢ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ

አዲስ አበባ፡- የአፍሪካ አሕጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት አጀንዳ 2063ን ተግባራዊ የሚያደርግ ነው ሲሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ያስሚን ወሃረቢ ገለጹ።

የአፍሪካ አሕጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ሴክሬቴሪያት ከፍተኛ የንግድ ባለሙያዎች ጉባኤ ከትናንት ጀምሮ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር የንግድ ትስስርና የወጪ ንግድ ፕሮሞሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ያስሚን ወሃረቢ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ጉባኤው አጀንዳ 2063 ተግራዊ የሚደረግበት ነው።

ጉባኤው በአሕጉሪቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የጋራ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የንግድ ትስስር የሚፈጠርበት ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ከጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ መቆየቱን ጠቁመዋል። በቀጣይም ከጥቅምት 30 እስከ ኅዳር 1 ቀን 2017 ዓ.ም የንግድ ሚኒስትሮች የጋራ ጉባኤ እንደሚደረግ አመላክተዋል። ስብሰባው ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚካሄድ መሆኑንም አስረድተዋል።

የአፍሪካ አጀንዳ 2063 አሕጉራዊ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እንዲሁም ማኅበራዊ እድገት ለማረጋገጥ ከታቀዱ ፕሮጀክቶች መካከል የአፍሪካ አሕጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት አንዱ ነው ብለዋል።

ዋና ዓላማውም በፓን አፍሪካን ራዕይ አሕጉራዊ የኢኮኖሚ ውሕደት በማስፋት የዕቃዎችና አገልግሎት ገበያን መፍጠር፣ የአፍሪካን ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የካፒታልና የሰዎችን ነፃ እንቅስቃሴ በማመቻቸት ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ፕሮጀክቱ በጥቅሉ ሦስት ነጥብ አራት ትሪሊዮን ዶላር ያላቸው ሀገራትን እና ከአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን በላይ የሆነውን ሕዝብ ጥቅል አሕጉራዊ የልማት ምጣኔን የሚያሳድግ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

ጉባዔው በሀገራችን መካሄዱ ኢትዮጵያ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ጀምሮ ለአፍሪካዊ ጉዳዮች ያላትን አጋርነት እንዲሁም ስምምነቱን እንደ ሀገር ለመተግበር ያላትን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ብለዋል። በተጨማሪም የንግዱ ማኅበረሰብና መላው ኅብረተሰብ በጉዳዩ ላይ ያለው ግንዛቤ ለመጨመር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ጉባኤው ለተከታታይ ሦስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን አንድ የአፍሪካ ገበያን የመፍጠር እሳቤ ያነገበ ስለመሆኑም ተጠቁሟል። የአፍሪካ አሕጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት እ.ኤ.አ  መጋቢት 21 ቀን 2018 በሩዋንዳ ኪጋሊ በተካሄደ የአፍሪካ ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ተፈርሞ በሚያዚያ 30 ቀን 2019 ተግባራዊ ሆኗል፤ እ.አ.አ. ከጥር 1 ቀን 2021 ጀምሮ ንግድ እንዲጀመር ስምምነት ላይ ተደርሷል።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን  ጥቅት 27/207 ዓ.ም

 

Recommended For You