“ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርገውን መንገድ በመምረጥ ችግሮችን በምክክር መፍታት ይገባል”የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፡– ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርገውን ሠላማዊ መንገድ በመምረጥ ችግሮችን በምክክር መፍታት ይገባል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ኢፕድ ያነጋገራቸው የጉጂ አባገዳ የሆኑት አባገዳ ጃርሶ ዱጎ እንደተናገሩት፤ ልዩነቶችን በሠላማዊ አካሄድ በምክክር መፍታት ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ተግባር ነው።

በሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ልዩነቶችን በሠላማዊ መንገድ መፍታት ይኖርበታል ያሉት አባገዳ ጃርሶ፤ ከመገፋፋት ይልቅ ችግሮችን በምክክር በመፍታት ሠላምን ማስፈን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የጉጂ፣ ሜጫ፣ ቱለማ፣ ሲኮ መንዶ፣ አባገዳዎችም መክረው በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ተሳታፊ መሆን እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ በምክክሩ ላይም መግባባትንና መቀራረብን ማምጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ለመምከር መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

ሠላም የሁሉም ነገር መሠረት በመሆኑ ችግሮችን በምክክር መፍታት ያስፈልጋል የምትለው ደግሞ ከጅማ ዞን ሊሙሰቃ ወረዳ የመጣችው ወጣት ራሃ ሙዘሚል ናት፡፡

ሁሉም ሰው ምክክር በማድረግ ወደ ሠላም መምጣት አለበት ያለችው ወጣት ራሃ፤ ምክክርን አማራጭ ማድረግ ልዩነቶችን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት እንደሚያስፈልግም ጠቁማለች፡፡

ልዩነቶችን በግጭት ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ በመምከር መፍታት ተገቢ ነው የሚሉት ደግሞ የጫንጮ ከተማ ነዋሪው አቶ ሞዳ ቦረናገዲ ናቸው፡፡

ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅመው ከግጭት ይልቅ በሠላማዊ መንገድ ምክክር በማድረግ ልዩነቶችን መፍታት ነው ያሉት አቶ ሞዳ፤ መግባባት፣ መመካከር፣ ወደ ሠላም መምጣት እና ችግሮችን በውይይት መፍታት አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ማንኛውም ሰው ያለውን ጥያቄ ማቅረብ ያለበት በሠላማዊ መንገድ መሆን እንዳለበት ጠቅሰው፤ ልዩነቶችንና ጥያቄዎችን ሀገራዊ ምክክርን በመጠቀም ወደ መፍትሔ፣ ሠላም፣ አንድነትና ልማት መምጣት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

ሀገራዊ ምክክር ችግሮቻችንን ለመፍታት ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ ሁሉም ሰው ይሄን ዕድል መጠቀም አለበት ያሉት አቶ ሞዳ፤ የትኛውም ሰው ያለውን አጀንዳ በሠላማዊ መንገድ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ማቅረብ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

የተለያዩ ሀገራት ምክክር አካሂደው ሀገራዊ መፍትሔ በማምጣት ችግሮቻችውን መፍታት መቻላቸውን ጠቅሰው፤ ምክክሩ ለሀገር ትልቅ መፍትሔ ይዞ መምጣት የሚችል በመሆኑ በንቃት እንደሚሳተፉ አንስተዋል፡፡

የአዳማ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ሄለን ከበደ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በሀገሪቱ ሠላማዊ ሁኔታን ለመፍጠር፣ መግባባትንና ፍቅርን ለማጠናከር ምክክር አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ምክክር የኢትዮጵያ ሕዝብ ተግባብቶ በሠላም አብሮ እንዲኖር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል የሚሉት ወይዘሮ ሄለን፤ ወጣቶች የሠላም ተምሳሌት በመሆን በሀገሪቱ ሠላምና አንድነት እንዲሰፍን የድርሻውን ሊወጡ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም የክልሉ ወጣቶች በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ልዩነቶችን በሠላማዊ መንገድ ሊፈቱ እንደሚገባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን  ጥቅት 27/207 ዓ.ም

 

Recommended For You