አዲስ አበባ:– የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድረው ያልመለሱትን ዕዳ ለመክፈል እና የባንኩን ካፒታል ለማሳደግ የሚውል የመንግሥት የቦንድ ሽያጭ እንዲወጣ የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ በአብላጫ ድምፅ አፀደቀ፡፡
ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንትና አራተኛ መደበኛ ስብሰባውን ሲያካሂድ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጫና የሚቀንስና ካፒታሉን ከፍ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ አፅድቋል።
ስለረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ያቀረቡት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወሰዱትን ብድር ለመክፈል ባለመቻላቸው በመንግሥት ዕዳ ሰነድ ወይንም ቦንድ እንዲከፈል ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሀገሪቱ የንግድ ባንክ እንቅስቃሴ ውስጥ የያዘውን ከፍተኛ ድርሻ ይዞ እንዲቀጥል ለማድረግ ደረጃ በደረጃ ካፒታሉን ማሳደግ ማስፈለጉን አመልክተዋል፡፡
የልማት ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወሰዱትን ብድር በወቅቱ ባለመመለሳቸውና የብድር ወለዱም በጣም ከፍ በማለቱ በባንኩ ላይ ከፍተኛ ጫና ማስከተሉንም አንስተዋል፡፡ ባንኩ የሀገሪቱ ዋነኛ የፋይናንስ ተቋም በመሆኑ በብድር የተወሰደው 900 ቢሊዮን ብር የመንግሥት ዕዳ ሰነድ ሆኖ እንዲከፈል መወሰኑን አስታውሰዋል።
በታቀደው መሠረት ዕዳውን ለመክፈል የሚያስችል በቂ የገንዘብ ምንጭ ሊገኝ ባለመቻሉና ዕዳው ሳይከፈል በመቆየቱ የወለድ ሂሳቡ የዕዳውን ጫና እያከበደው በመሄድ ላይ እንደሚገኝ በመጠቆም ርምጃ መውሰድ ማስፈለጉን ተጠሪ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከብር 845 ቢሊዮን 316 ሚሊዮን ብር በላይ ያልተሰበሰበ ሂሳብ ይዞ መቆየቱ በባንኩ የፋይናንስ ገጽታ ላይ አሉታዊ ውጤትን በማስከተሉ ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችል ርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል፡፡
የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በፈጠሩት ችግር ተግዳሮት ውስጥ ያለውን ባንክ ለመታደግ ምክር ቤቱ ኃላፊነት ሊወስድ እንደሚገባው፣ የቦንድ ሽያጩን አካሂዶ ወደ ጤናማ አቋም መመለስ ተገቢ በመሆኑ አዋጁን እንደሚደግፉት ተናግረዋል፡፡
የልማት ድርጅቶቹ የሕዝብን ጥያቄ በብቃት የማይመልሱ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር ያለባቸው፣ ሀገርን ለከፍተኛ ዕዳ የዳረጉ በመሆናቸው የአስተዳደር ችግር ሁኔታቸው ጭምር ታይቶ በተጠና መንገድ ውሳኔ ሊያገኙ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ለዚህም ተቋማቱን የሚከታተላቸው ቋሚ ኮሚቴ የልማት ድርጅቶቹ ያሉበትን ሁኔታና ከገቡበት ችግር የሚወጡበት መንገድ በዝርዝር አጥንቶ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል፡፡
የስኳር እና የማዳበሪያ ፋብሪካዎች በሚል እንደትልቅ እመርታ ሲጠቀሱ የነበሩ ተቋማት ሃገራዊ ውድቀት ማስከተላቸው አንድምታው ሊብራራ እንደሚገባ አንስተው፤ ከለውጡ በፊትም ሆነ በኋላ በሀገር ሀብት ብክነት ዙሪያ ተጠያቂነት ሊሰፍን ይገባል ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፤ የልማት ድርጅቶቹ ከፍተኛ የአሠራር ችግር የነበረባቸውና ሳይጠኑ ወደሥራ የገቡ እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡ ተቋማቱን ለማስተካከልና ዕዳውን ወደ ምንዳ ለመቀየር ባለፉት ስድስት ዓመታት በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውንም ገልጸዋል፡፡
በትግበራው በርካታ ተቋማት ከነበሩበት አዘቅት ወጥተው ወደትርፋማነት መሸጋገራቸውን ጠቁመው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድና ኢትዮ ቴሌኮም በአሕጉር ደረጃ ጭምር ተወዳዳሪ መሆን መቻላቸውን አንስተዋል፡፡
አሁን የተነሳው ያደረና የከረመ ችግር ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተወስዶ ሳይከፈል የቀረ ዕዳ በዚህ ደረጃ ከፍ ያለው በየጊዜው ሊከፈል ባለመቻሉና ወለዱ እየጨመረ በመሄዱ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ጉዳዩን ከመሠረቱ ለመፍታት በመጀመሪያ ዙር የዕዳ እና ሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን በማቋቋም ዕዳውን እንዲተላለፍ በማድረግ በርካታ ተቋማት ዕዳቸው ተሻሽሎ ጊዜያዊ መፍትሔ ማግኘታቸውንም ተናግረዋል፡፡
ዘላቂ መፍትሔ እንዲገኝ ለማድረግ ጉዳዩን ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር በመውሰድ በብድር ሰነድ መክፈሉ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን የገለጹት እዮብ (ዶ/ር) እንዲህ አይነቱ ሁኔታ በጭራሽ እንዳይደገም የልማት ድርጅቶቹ የሚመሩበት ሁኔታ በመሠረታዊነት መቀየሩንም አመልክተዋል፡፡
በተጨማሪ ምክር ቤቱ የዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ኮንቬንሽን ማሻሻያንና ኢትዮጵያ ከማልታና ከቻድ ሪፐብሊክ መንግሥታት ጋር ያደረገቻቸውን የአየር አገልግሎት ስምምነት ረቂቅ አዋጆች አፅድቋል።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ጥቅት 27/207 ዓ.ም