የዓለም መድኃኒት ድርጅት እ.ኤ.አ በ2019 ያወጣው መረጃ እንደሚያመላክተው ከሰባት ሰዎች መካከል አንዱ የሱስ ተጠቂ ነው፡፡ በኢትዮጵያን በተማሪዎች ላይ የሚስተዋለውን ሱስ አስያዥ ዕፅ አጠቃቀምን በተመለከተ እ.ኤ.አ በ2021 በተጠናው ጥናት በአፍላ እድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ወጣቶች ዘንድ የሱስ አምጪ ንጥረ ነገሮች ተጠቃሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡
በጥናቱ እንደተገለጸው፤ ሱሰኝነት በይበልጥ በሁለተኛ ደረጃና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ዘንድ ተስፋፍቷል፡፡ ወጣቶቹ በተለይ አዕምሮን ለማንቃት ብለው የሚጠቀሟቸው ንጥረ ነገሮች (Psychoactive Substances) ለከፍተኛ የጤና ችግር አልፎም ሞትን ለሚያስከትሉ በሽታዎች እያጋለጣቸው እንደሚገኝም በጥናቱ ተቀምጧል፡፡
ሱሰኝነት አንድን ወይም የተለያዩ ሱስ አምጪ ንጥረ ነገሮችን (ትምባሆ፣ መጠጥ፣ አበረታች መድኃኒት እና ጫት) በተደጋጋሚ መጠቀምና የንጥረ ነገሮቹ ጥገኛ የመሆን ችግር ነው። እነዚህን ንጥረ ነገሮች አንድ ሰው በገዛ ፈቃዱ ቢጀምራቸውም በጊዜ ሂደት ግን አዕምሮውን፣ ጊዜውን አካሉን የሚቆጣጠሩ የራሳቸው ጥገኛ የማድረግ ባሕርይ ስላላቸው ለማንኛውም በሱስ ለተጠቃ ሰው እንደ ጅማሮው ቀላል አይሆንለትም። ሱሰኝነት የአዕምሮ ጤናን የሚያውክ ማኅበራዊ ቀውስንም የሚስከትል ሲሆን ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሱስ ሊገቡ ይችላሉ። ስለሱስ ተያያዥ መዘዞቹና መፍትሔዎቹ ያነጋገርናቸው የዘርፉን ባለሙያዎችም በጉዳዩ ዙሪያ አመክንዮታዊ ሃሳባቸውን አቅርበውልናል።
ሲስተር ይርገዱ ሀብቱ አዲስ ሕይወት የተሰኘ የዕፅና አልኮል ሱሰኝነት ሕክምናና ማገገሚያ ማዕከል መሥራች ናቸው። ለሱስ አጋላጭ ምክንያች በርካታ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
እርሳቸው እንዳሉት፤ 10 ሰዎች ወደ ሱስ የገቡበትን ምክንያት ቢጠየቁ 10 ዓይነት ምክንያት ሊናገሩ ይችላሉ። በተለይ በአቻ ግፊት፣ በግንዛቤ ችግር፣ መዝናናት በሚል ሰበብ፣ ለጥናት ይጠቅማል በሚል፣ ከአቅም በላይ ሠርቶ ገንዘብ በማግኘት፣ ሥራ በማጣት፣ ገንዘብ በማጣት፣ በትዳር እና በቤተሰብ መካከል በሚፈጠር ችግር፣ በቤተሰብ መካከል ሱስ አምጪ ንጥረ ነገር ተጠቃሚ በመኖሩ፣ በሕይወት ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን ወይም ፈተናዎችን ለመሸሽ ወይም ጊዜያዊ ችግሮችን ለመርሳት የሚሉና እና ሌሎችም ወደ ሱስ ከገቡ ሰዎች ከሚደመጡ ምክንያቶች መካከል በዋናነት ይጠቀሳሉ።
በአቻ ግፊት ወደ ሱስ ሕይወት እንደገባ ያጫወተን የ29 ዓመቱ ወጣት ተካልኝ ክበበው፤ መጀመሪያ ሲጋራ ያጨሰው በ16 ዓመቱ እንደነበር ያስታውሳል። በዚያን ወቅት በዕድሜ ያልበሰለበት፣ ሲጋራ ማጨስ እንደ አራዳነት የሚቆጠርበት
ጊዜ እንደነበር ይናገራል። “እንደ ቀልድ ከጓደኞቼ ጋር እየተቀባበልኩ የጀመርኩት ሲጋራ ወደ ጫትና አልኮል ተጠቃሚነት ተሻግሮ ሕይወቴን አበላሽቶብኛል” ይላል።
ወጣቱ እንደነገረን ቤተሰቦቹ ጥሩ ገቢ ያላቸው የሚያስፈልገውን ብቻ ሳይሆን የሚጠይቀውን ሁሉ የሚያደርጉለት ነበሩ። የእርሱ ወደ ሱስ መግባትና ከቤተሰቡ ትዕዛዝ መውጣት በወላጆቹ መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር እንዳደረገም ያስታውሳል። በእናትና በአባቱ መካከል ለእሱ መበላሸት አንዳቸው አንዳቸውን ሲከሱ የሚፈጠረው ጭቅጭቅና ሠላም ማጣት በጊዜው ለእርሱ ምንም ትርጉም ይሰጠው እንዳልነበረም ይጠቁማል።
ከሱስ ሕይወት ለመውጣት ፍላጎት ቢኖረውም፣ ከሱስ ጥገኝነት መላቀቅ ባለመቻሉ በመኖሪያ አካባቢው በሚገኝ ኤምባሲ ፊት ለፊት ጉዳይ ለማስፈፀም የሚመጡ ሰዎችን መኪና በመጠበቅና መረጃ በመስጠት በሚያገኘው ሳንቲም እና ቤተሰቦቹ በሚሰጡት ገንዘብ በመያዝ የሱስ ፍላጎቱን ያሟላል።
በእኔ ተስፋ ያልቆረጠችው እናቴ ብቻ ናት ያለው ወጣት ተካልኝ፤ አባቱ እነርሱንም ያበላሻል በሚል ከታናናሽ ሁለት ወንድሞቹ ጋር እንኳ እንዲቀራረብ እንደማይፈልግ በኃዘን ስሜት ይናገራል። ምግብ ላይ ብዙም አይደለሁም ያለው ወጣቱ በተለይ ሳንባው ክፉኛ እንደተጎዳና ሲጋራ ማጨሱን የማያቆም ከሆነ ለከፋ ችግር እንደሚያጋልጠው በሐኪም እንደተነገረው ይገልጻል።
ሲስተር ይርገዱ በበኩላቸው፤ የሱስ ጥገኛ የሆኑ ሰዎች፤ ምንም ያህል ገንዘብና ጥሩ ገቢ ቢኖራቸው ገንዘብ መያዝ ካለመቻላቸውም ባለፈ ያላቸውንም እያጡ እንደሚሄዱ ይናገራሉ። እንዲህ አይነት ኑሮን ያሳለፉ ከሱሰ የተነሳ ከቤተሰቦቻቸው የተጋጩና የተለያዩ፣ ትዳራቸው የተበተነ፣ ትምህርትና ሥራቸውን ያጡ፣ ኢኮኖሚያቸው የተጎዱ በርካታ የሱስ ተጠቂዎች መኖራቸውንም ያነሳሉ።
ሱስ የራስ ሕይወትን ከማቃወስ ጀምሮ ቤተሰብን የሚያወክ፣ ማኅበራዊ ተቀባይነትንም የሚያሳጣ እንደሆነ የሚናገሩት ሲስተር ይርገዱ፤ ማኅበረሰቡ ሱስ ታክሞ መዳን የሚችል በሽታ መሆኑን ባለመረዳቱ በሱስ የተጠቁ ሰዎችን ዝቅ አድርጎ የማየት፤ የማይረቡ አድርጎ የመመልከት ሁኔታ እንዳለ ያስረዳሉ። ይህ አይነቱ የማኅበረሰቡ ዕይታ በሱስ የተጠቁ ሰዎችም ራሳቸውን የማይረቡ አድርገው እንዲቆጥሩ እንደሚያደርጋቸውም ያስረዳሉ።
ሱሰኝነት በግለሰቡ ላይ ከሚያስከትለው የጤና ችግርና ማኅበራዊ ቀውስ ባለፈ በሀገር ላይም አሉታዊ ውጤትን የሚያስከትል ነው ያሉት ሲስተር ይርገዱ፤ በሀገራችን እየጨመረ የመጣው የትራፊክ አደጋና ልዩ ልዩ አይነት ወንጀሎች በአብዛኛው ከሱስ ሕይወት ጋር ተያያዥነት እንዳላቸው ይጠቅሳሉ።
ማዕከላቸው ከሱስ ሕይወት ማላቀቅ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን የተናገሩት ሲስተር ይርገዱ፣ ቅድመ መከላከል ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት ይገባል ይላሉ። አንድ ሰው ወደ ሱስ ጥገኝነት እየተጓዘ መሆኑን ከተረዳን፣ ይህ ሰው ጤናው ከመታወኩ፣ ስርቆት ውስጥ ከመግባቱ፣ ጎዳና ላይ ከመውጣቱ፣ ሌሎችንም ችግሮች ከመፈጠራቸው አስቀድሞ ርዳታ ወደሚያገኝበት የማገገሚያ ማዕከላት መውሰድ እንደሚገባም ያሳስባሉ። ግለሰቡ ለመለወጥ ከቆረጠ ከሱስ መላቀቅ ይቻላል ያሉት ሲስተር ይርገዱ፣ ሱሰኝነት ታክሞ መዳን የሚችል በሽታ ነው የሚለው ላይ አፅንዖት ሰጥተዋል።
ዮርዳኖስ ፍቅሩ
አዲስ ዘመን ጥቅት 27/207 ዓ.ም