ከመኸር እርሻ 615 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡- ከ2016/17 ዓ.ም የመኸር እርሻ 615 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየተሠራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ከበደ ላቀው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በ2016/17 ዓ.ም የመኸር እርሻ በሁሉም ክልሎች 20 ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ሙሉ ለሙሉ በዘር በመሸፈን 615 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት የታቀደውን እቅድ ተግባራዊ በማድረግ የደረሱ ሰብሎችን በሰው ኃይልና በኮምባይነር የመሰብሰብ ሥራ እየተሠራ ነው።

በ2016/17 ዓ.ም የመኸር እርሻ በዘር ለመሸፈን የታቀደውን 20 ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ሙሉ ለሙሉ በዘር የመሸፈን ሥራን በማሳካት 615 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት በቆላና በደጋ የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰብ፤ ያልደረሱ ሰብሎች አስፈላጊውን እንክብካቤ የማድረግ፤ ሲደርሱ በጊዜያቸው እንዲሰበሰቡ ተገቢውን ዝግጅት የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በሀገሪቱ የተለያዩ ቆላማ አካባቢዎች የደረሱ ሰብሎችን በሰው ኃይልና በኮምባይነር የመሰብሰብ ሥራ እየተሠራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። በ2016/17 ዓ.ም የመኸር እርሻ ከ20 ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬትን በበቆሎ፤ በማሽላ፣ በስንዴ፤ በጤፍ፣ በገብስና በመሳሰሉ ሰብሎች የመሸፈን ሥራ ተሠርቷል፤ ከተዘሩት የተለያዩ ሰብሎች ውስጥ የደረሱ ሰብሎችን በጊዜያቸውና በወቅታቸው የመሰብሰብ ሥራ በስፋት እየተሠራበት መሆኑን ተናግረዋል።

የምርት ብክነት እንዳይደርስ የደረሱ ሰብሎችን በጊዜያቸው፤ በወቅታቸው፣ በጥንቃቄ በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ ማለትም በግብርና መካናይዜሽን በመሰብሰብ ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የደረሱ ሰብሎችን ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንዳያበላሻቸው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የሚትዎሮሎጂ ተቋም ጋር በቅንጅት በመሥራት ለአርሶ አደሩ መረጃ በፍጥነት እንዲደርሰው የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑንና አርሶ አደሩም ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግ ሰብሎችን በጊዜያቸው የመሰብሰብ ሥራ እየሠራ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ግብርናውን የማዘመን፣ ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ እየተሠራ ነው፤ እየተሠራ ያለውም ሥራ ትልቅ ውጤት እያስገኘ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ በኩል እያነሳ ያለውን ንቁ ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You