የሃይማኖት ተቋማት የመቻቻል ትርክትን መገንባት ላይ መሥራት እንዳለባቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፡- የሃይማኖት መሪዎችና ተቋማት የመቻቻል ትርክትን መገንባትና የተዛባ አመለካከትን ማረም ላይ ሊሠሩ እንደሚገባ ተገለጸ።

የሠላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዱዓለም በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ የሃይማኖት ተቋማት የመቻቻልን ትርክት ሊያበረታቱና ዜጎች በመተሳሰብ እንዲኖሩ ቁልፍ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል።

ሃይማኖት የግለሰቦችንና የማኅበረሰቦችን እሴትና ባሕሪን የመቅረጽ አቅም ያለውና በተከታዮች ዘንድም ትልቅ ዋጋ ያለው ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ ሆኖም ግን በሃይማኖት ልዩነቶች ምክንያት በማኅበረሰቡ ዘንድ ብዙ መከፋፈሎችና ግጭት ሲነሳ ይስተዋላል ብለዋል።

ሃይማኖት የአንድነትና የጥንካሬ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ሁሉ ጥላቻንና ግጭትን ሊያበረታታ እንደሚችል ጠቅሰው፣ የተለያዩ አጥፊ ኃይሎች የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት የማኅበረሰቡን ሠላም ሲያደፈርሱ እንደሚስተዋልም ገልጸዋል።

ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት የመቻቻልን ትርክት ሊያበረታቱና ዜጎች በመተሳሰብ እንዲኖሩ ማድረግ ተገቢ መሆኑን በመግለጽ፤ ተቋማቱ መንፈሳዊ ድጋፍን በማድረግ በማኅበረሰቡ ዘንድ አንድነትን በማበረታታት ቁልፍ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፣ ተቋማት ከምን ጊዜውም በላይ ተቀራርበው ለሰው ልጆች አንድነት፣ መከባበርና ሠላም በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

ልዩነቶች እንደተጠበቁና እንደተከበሩ ሆነው ዜጎች በመቻቻልና በመከባበር በሠላም ይኖሩ ዘንድ የሃይማኖት አባቶች ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ያሉት ፀሐፊው፤ በዓለም ላይ የሚስተዋሉ አሳዛኝ ክስተቶችንና ሰቆቃዎች ለማስቆም የእረኝነት ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

ችግሮችን ለማስወገድ አብሮ መኖርን፣ መቻቻልን፣ ፍትሕን ማስፈንን ጨምሮ፣ እኩልነትና ነፃነት ላይ በማተኮር መሥራት አስፈላጊ መሆኑን እና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት፣ የተሳሳተ ትርክት፣ የኢ-ፍትሐዊነትና የእኩልነት እጦት ውጤት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከሃይማኖት አስተምሮም ሆነ ከሰብዓዊ ድንጋጌዎች አንጻር ሁሉም ሰው እኩልና የተከበረ ፍጡር ነው ያሉት ቀሲስ ታጋይ፤ ለደሀውና ለተቸገረው በእውነት መፍረድ፣ ለተገፋው ማዘን የሃይማኖት መመሪያና ግዴታ ነው ብለዋል።

ሁሉም ሃይማኖቶች ሠላምን፣ አንድነትን፣ ፍቅርን መረዳዳትን እንዲያስተምሩና እንዲሰብኩ ከፈጣሪ የተሰጣቸው ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰው፣ መለያየት ኃጢያት መሆኑን የሃይማኖት አባቶች በቃልና በተግባር በተከታዮቻቸው ማስገንዘብ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

የመሐመድ ቢን ዛይድ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ከሊፋ ሙባረክ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ የጥላቻ ትርክትን በማስወገድ የአንድነት እሴቶችን ማሳደግ ያስፈልጋል።

በሃይማኖት ተቋማት መካከል የመነጋገር ባሕልን ማሳደግ አስፈላጊ ነው ያሉት ከሊፋ (ዶ/ር)፣ ተቋማቱ ልዩነቶችንና ግጭቶችን ለማስወገድ ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል ብለዋል።

በሃይማኖቶች መካከል መቻቻልና አብሮ መፍጠር ለሠላም እወጃ በር የሚከፍት መሆኑን ጠቅሰው፤ በሕዝቦች መካከል ልባዊ የሆነ አንድነትን ለመፍጠር ተቋማቱ በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።

የሠላም ሚኒስቴርና የመሐመድ ቢን ዛይድ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You