የኢኮኖሚ ማሻሻያው አልሚዎች ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች መፍትሔ እየሰጠ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፡– በመንግሥት የተወሰዱ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች አልሚዎች ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች መፍትሔ እየሰጠ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

ኮርፖሬሽን የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽንና ማርኬቲንግ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘመን ጁነዲን እንደገለጹት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት መንግሥት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለሚያለሙ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በርካታ ማበረታቻዎችን አድርጓል። በመንግሥት የተወሰዱ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች አልሚዎች ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች መፍትሔ እየሰጠ ነው።

ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብተው ለማልማት ችግር ነበረባቸው ያሉት አቶ ዘመን፤ የምንዛሪ እጥረቱ በመቀረፉ ለአልሚዎች ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችም በመላ ሀገሪቷ በሚገኙ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በስፋት እየተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለይ በጨርቃጨርቅ፣ በግብርና ማቀነባበር፣ በፋርማሲቲካል፣ በመኪና መገጣጠሚያና በሌሎች ዘርፎች የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች መሠማራታቸውን ገልጸዋል። እንዲሁም በተደረገላቸው ትንሽ ድጋፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን መቻላቸውንም አመልክተዋል።

እንደ አቶ ዘመን ገለፃ፤ መንግሥት የወሰዳቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ጨምሮ ከውጭ ምንዛሪ ጋር ያለውን ችግር መፍታት በመቻሉ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍላጎት ጨምሯል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የቻይናና የአሜሪካ ባለሀብቶች የለማ መሬት ወስደዋል። በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ካሉ ሼዶች ውስጥ 86 በመቶ በአልሚዎች ተይዘዋል። የኢንቨስትመንት መዳረሻዎችን ከብሪክስ ሀገራት ጋር የማስፋት ሥራ እየተሠራ ሲሆን ከአባል ሀገራቱ በርካታ ባለሀብቶች ወደ ኢንቨስትመንት ለመግባት በሂደት ላይ ናቸው።

የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ኢንቨስትመንትን ከማነቃቃትና ከሚፈጥሩት የሥራ ዕድል በተጨማሪ ተኪ ምርቶች ላይ ትልቅ አስተዋፅዖ እያደረጉ መሆኑን በመጥቀስ፤ የተዛባውን የወጭና የገቢ ንግድ በማስተካከል ረገድ ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል።

በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ ይገባ የነበረውን የፀጥታ አካላት አልባሳትን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉ በማሳያነት ጠቅሰዋል። በተጨማሪም ለቢራ አገልግሎት የሚውለውን የገብስ ብቅል በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉ ባሌና አርሲ ለሚገኙ 60 ሺህ አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአካባቢው ያለውን አቮካዶ በማቀነባበር 30 ሺህ ለሚደርሱ አምራቾች የገበያ ትስስር ፈጥሯል ያሉት ምክትል ሥራ አስፈጻሚው፤ ከአቦካዶ ዘይትና ቅባት በማምረት ለአውሮፓና ለአሜሪካ ገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በዚህም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እየተገኘ መሆኑን አመልክተዋል።

በባሕርዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከአኩሪ አተር የምግብ ዘይት በማምረት ሙሉ ለሙሉ ለውጭ ገበያ የማቅረብ ሥራ መጀመሩን ጠቅሰው፤ በዚህም ዘጠኝ ሺህ ስምንት መቶ ለሚደርሱ አርሶ አደሮች ዘላቂ የገበያ ትስስር መፍጠር መቻሉን አስረድተዋል።

በፓርኮች የተሰማሩ አልሚዎች የኢንቨስትመንት ምሕዳሩን ከማነቃቃት በተጨማሪ የተኪ ምርት ላይ አስተዋፅዖ እያደረጉ ነው ያሉት አቶ ዘመን፤ ይህም እንደ ሀገር ለታሰበው የመዋቅራዊ ሽግግር ዋነኛ ተዋናይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ኢንዱስትሪያሊስቶች እንዲፈጠሩ ማድረጉን ጠቁመዋል። ፓርኮች በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የውሃ አቅርቦት የተሟላላቸውና ደኅንነታቸው የተጠበቀ በመሆኑ ከሌሎች የኢንቨስትመንት ማዕከላት ተመራጭ ስለመሆናቸው ገልጸዋል።

ሞገስ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You