አዲስ አበባ፡– የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር በመመደብ በአራቱም ክልሎች የቡና ምርት ለማዘመን የግብዓት አቅርቦት ማከፋፈሉን ገለፀ።
የባለሥልጣኑ ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር)፤ ባለሥልጣኑ አርሶ አደሩን ለማገዝ ከመደበው ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ሦስት ሚሊዮን የቡና ማምረቻ ዘመናዊ መቆፈሪያ ማሽኖች፣ ዘመናዊ መጋዝ የቡና መጎንደያ (መቁረጫ) እና ሌሎች ግብዓቶች በመግዛት ለአራቱም ክልሎች፤ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ አርሶ አደሮች ማስረከቡን ገልፀዋል።
በተለይ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን ሥራዎች ለመሥራት ከመንግሥት በሚገኘው ገቢ ብቻ በቂ ስለማይሆን ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ገቢ በማፈላለግ ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰው፤ ፕሮጀክቱ በዋናነት ለአርሶ አደሩ ሥልጠና መስጠት፣ ግብዓትን ማቅረብ እና የኤክስቴንሽን ተደራሽነትን ለማስፋት ተብሎ የተቀረፀ መሆኑን አመልክተዋል።
ለፕሮጀክቱ ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር መመደቡን ገልፀው፤ የተመደበው ዶላር ከተባበሩት መንግሥታት ልማት ድርጅት (UNDPR) መገኘቱን አመልክተዋል። ሦስት ሚሊዮን ዶላሩ ወደ ባለሥልጣኑ አካውንት ገቢ የተደረገ በመሆኑ አንድ ሺ ሦስት መቶ ስማርት ስልክ በመግዛት የገበሬው የቡና ማሳ ሎኬሽን ማሳያ እንዲያገለግል መሰጠቱንም ተናግረዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ የአራቱም ክልሎች ማለትም ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ሲዳማ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስፈልጋቸውን በቴክኖሎጂ የታገዙ ግብዓቶች እንዲገዙ ተደርገዋል። ያረጁ የቡና ተክሎች አንስቶ በአዲስ በመተካት ምርት እና ምርታማነት ለማሳደግ እንቅስቃሴ ተደርጓል።
ከዚህ ቀደም አርሶአደሩ ያረጁ ቡናዎችን ለማንሳት የሚጠቀምበት መሣሪያ ኋላቀር በመሆናቸው ከአንዱ ቡና ወደ ሌላኛው ቡና በሽታዎች በቀላሉ ይተላለፉ እንደነበር ጠቁመዋል። ቡናውንም ለመቁረጥ ብዙ ጉልበት ይፈጅ እንደነበር በመጥቀስ፤ ይህን ለማስቀረት አዳዲስ የመጎንደያ (የመቁረጫ) ማሽን ለአርሶ አደሮች መሰጠቱን ጠቁመዋል።
አጠቃላይ አንድ መቶ ሠላሳ አንድ ሚሊዮን ብር በማውጣት ለአራቱም ክልሎች ግብዓቶች የተገዛ ሲሆን፤ ሁለት መቶ ሃያ አምስት ሞተራይዝድ መጋዝ፣ ሁለት መቶ ሃያ ዘመናዊ የጉድጓድ መቆፈሪያ፣ አስር ሺ የተጎነደለ ቡና ለመቀጠል የሚረዳ ማሽን እና ሌሎች ግብዓቶች መቅረባቸውን ገልፀዋል።
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26 ቀን 2017 ዓ.ም