አዲስ አበባ፦ በአረንጓዴ ዐሻራ የተተከሉ ችግኞች ለቀጣናው ዘላቂ የውሃ ሀብት ልማትና አስተዳደር ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከቱ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሃይድሮሜት ኮንፈረንስ “አረንጓዴ ዐሻራ፣ ለዘላቂ ቀጣናዊ የውሃ ሀብት አስተዳደር ያለው እመርታ” በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት ተካሂዷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በወቅቱ እንደገለፁት፤ የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም ላይ ጎርፍና ድርቅ እንዲሁም ሌሎች ጉዳቶችን እያደረሰ ይገኛል። በዚህም ከሚያደርሰው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ባለፈ ሕይወት እየቀጠፈ ነው።
መድረኩ ሀገራችን በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ያስመዘገበቻቸውን አመርቂ ድሎች በአሕጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረው፤ በኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች መተከላቸውን ገልፀዋል።
በዚህም አጠቃላይ የደን ሽፋን አድጓል፣ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር የውሃ መጠን ጨምሯል፣ የአፈር መሸርሸር መጠን ቀንሷል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ችግኞችን የምንተክለው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ ጉዳቶችን ለመቅረፍ ነው ብለዋል።
ላለፉት ስድስት ዓመታት ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን በመቅረጽ እስከ ዛሬ ድረስ አርባ ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን ጠቅሰዋል። እነዚህ የተተከሉ ችግኞች ከከባቢ የአየር ሁኔታ፤ ምግብ ዋስትና እና የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ለቀጣናው ዘላቂ የውሃ ሀብት ልማትና አስተዳደር ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከቱ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በሃይድሮሜትሪ እና የቅድመ ማስጠንቀቂያ አገልግሎቶች ላይ የክልላዊ ትብብር፣ የአቅም ግንባታ እና የእውቀት ልውውጥ ላይ ትኩረት ሰጥታለች ብለዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለውሃ መጠን መጨመር ጉልህ ሚና አለው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ችግኞች በተተከሉ ቁጥር አካባቢው ላይ የሚደርሰውን የመሬት መራቆት ይቀንሳል፤ የደን ሽፋንን ያሻሽላል፣ የግድቦችንም እድሜ ያራዝማል እና የውሃው መጠን እንደሚጨምር ጠቁመዋል።
ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በዓባይ ተፋሰስ ችግኞች መተከላቸው የምንጮችን መጠን እንደሚጨምር እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል። ይህም የወንዞች መጠን እንዲጨምር በማድረግ ለኢትዮጵያም ብቻ ሳይሆን ለታችኛው የዓባይ ተፋሰስ ሀገሮችም እንደሚጠቅም ተናግረዋል።
የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬትስ ብሔራዊ የአየር ትንበያ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር እና የዓለም ሜትዎሮሎጂ ድርጅት ፕሬዚዳንት አብዱላ አሕመድ አል ማንዱስ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፤ እ.ኤ.አ. 2023 ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎች የታዩበት ዓመት ነበር። ከቀደምት ሪከርዶች ብልጫ የተመዘገበው ሞቃታማው ዓመት መሆኑ ተረጋግጧል።
እንደ ጎርፍ፣ ድርቅ፣ ሰደድ እሳት እና ኃይለኛ አውሎ ነፋሶች ያሉ አስከፊ የአየር ሁኔታ ክስተቶች በዓለም ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሳቸውን ገልጸዋል። የአየር ንብረት ለውጥን ለመቅረፍ እና ከሚያስከትላቸው ተፅዕኖዎች ጋር ለመላቀቅ አስቸኳይ ዓለም አቀፍ እርምጃ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ፤ ሳይንሳዊ ማስረጃው ግልፅ ነው። ምድራችንን እና የወደፊት ትውልዶቻችንን ለመጠበቅ የአየር ንብረት-ተከላካይ መፍትሔዎች ላይ ኢንቨስት ማድረግ አለብን። የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ የአየር ንብረት ለውጥን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያደረገ ነው።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26 ቀን 2017 ዓ.ም