ኢንተርፕራይዞቹ ለሀገር ኢኮኖሚ ልማት አስተዋፅዖዋቸውን ሊያሳድጉ ይገባል

አዲስ አበባ:- አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በአዕምሯዊ ንብረት ዘርፍ ያላቸውን ግንዛቤ አሳድገው ለሀገር ኢኮኖሚ ልማት የሚያበረክቱትን አስተዋፅዖ ከፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን አስታወቀ።

የአዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ከዓለም አቀፉ የአዕምሯዊ ንብረት ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የአዕምሯዊ ንብረት ሳምንት ትናንት ተከፍቷል።

በመርሐ ግብሩ መክፈቻ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ወልዱ ይመስል እንዳሉት፤ በኢኮኖሚ ያደጉ ሀገራት አሁን ለደረሱበት ደረጃ በአዕምሯዊ ዘርፍ ልማት ጠንክረው በመሥራታቸው ምክንያት ነው። በትግበራው ጃፓን፣ ታይዋን፣ ደቡብ ኮሪያ በዘርፉ በቀዳሚነት የሚገለጹ ሀገራት መሆናቸውንም በአብነት ይጠቀሳሉ።

ሀገራቱ የመጀመሪያው የእድገት ጉዟቸው ከሀገራዊ ምርታቸው እስከ 90 በመቶ በእነዚህ ተቋማት ተመርቶ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ የሚቀርብበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰዋል። ኢንተርፕራይዞቹ ለወጣቱ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከታቸውንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሁለተኛው ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ በመጥቀስ፤ ዘርፉ የሀገር ኢኮኖሚን የሚለውጥበት ምቹ ሁኔታ እንዳለው አመልክተዋል።

ነገር ግን ኢንተርፕራይዞቹ ተሳትፏቸው ዝቅተኛ በመሆኑ ተቋማቱ በአዕምሯዊ ንብረት በተንቀሳቃሽ ሃብት ረገድ በትኩረት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በአዕምሯዊ ንብረት ዓለም በዘርፉ የደረሰበትን ደረጃ በመገንዘብ ኢንተርፕራይዞቹ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

በአዕምሯዊ ንብረት ሥርዓት መመዝገባቸው የገበያ ተወዳዳሪነትን በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድግላቸዋል፣ የምርት ዋጋን ይጨምራል፣ የገንዘብ ችግራቸውንም እንደሚፈታ ተናግረዋል። የፈጠራ ባለሙያዎች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን አስይዘው የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙበት ሥርዓት እየተገነባ እንደሚገኝ በመጠቆምም፤ ብዙ ባንኮች እንዲጠቀሙበት እንፈልጋለን ብለዋል።

በኢንተርፕራይዞቹ ጥራት ያላቸው ምርቶች እንዲመረቱ እና ምርቶቹ ዓለም አቀፍ ተፈላጊ እንዲሆኑ ማገዝ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ጳውሎስ በርጋ ኢንተርፕራይዞቹ ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጠራና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ጉልህ አስተዋፅዖ እያበረከቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል። አጠቃላይ 74 ቢሊዮን ብር ካፒታል ማስመዝገባቸውን፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን፣ በሃገር ምርት መኩራት እንዲቻል እንዲሁም በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር አስተዋፅዖ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

የዓለም አቀፉ የአዕምሯዊ ንብረት የአፍሪካ ተወካይ ዳይሬክተር ሚስ ሎሬታ በበኩላቸው፤ መካከለኛ እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በሀገራዊ ምርት እና ሁለንተናዊ ልማት ወስጥ ከፍተኛ ሚና እንደሚያበረክቱም ተናግረዋል።

እንደርሳቸው ገለጻ፤ አዕምሯዊ ንብረት ለኢንተርፕራይዞቹ ሥራቸውን ለማቀላጠፍ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው። የራሳቸው ብራንድ እንዲኖራቸው እና ዓለም አቀፍ የገበያ ተደራሽነት እንዲኖራቸው ለማስቻልም ጉልህ አስተዋፅዖ ያበረክታል።

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You