ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሀገራት ዶላርን ገሽሽ በማድረግ በራሳቸው ገንዘብ የመገበያየት (Currency swap) ስምምነቶች መፈራረማቸውን የሚገልጹ ዜናዎች መስማት እየተለመደ መጥቷል። በተለይም የብሪክስ አባል አገራት ይህን ስምምነት ተፈራርመው በራሳቸው ገንዘብ ግዙፍ የንግድ ልውውጦችን እያካሄዱ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያም ቁልፍ ከሆኑት የልማት አጋሮቿ የተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶች እና ቻይና ጋር ተመሳሳይ ስምምነት መፈራረሟ ይታወሳል። ለመሆኑ ሀገራት በራሳቸው ገንዘብ መገበያየትን እየመረጡ ያሉበት ምክንያት ምንድን ነው? ኢትዮጵያ እንዲህ ያለውን ስምምነት መፈረሟ የሚኖረው ፋይዳስ ምን ይመስላል ?
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በርሔ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማግስት የዓለም ኢኮኖሚን ለማረጋጋት በሚል እ.አ.አ በ1944 የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ሲቋቋሙ ሀገራት በምን ይገበያዩ የሚል ጥያቄ ተነሳ። በወቅቱ አንድ ሀገር ከሌላ አገር የሚገበያየው በወርቅ ነበር። የሁለቱን ድርጅቶች መመሥረት ተከትሎ በወርቅ ክፍያ ከመፈጸም
ይልቅ ወርቅን መሠረት በማድረግ (Gold standard) በመመሥረት ከፍተኛ የወርቅ ክምችት ያለው ማዕከላዊ ባንክ ገንዘብ በዓለም አቀፍ ደረጃ መገበያያ ይሁን የሚል ውሳኔ ላይ ተደርሷል።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንግሊዝን ጨምሮ አብዛኞቹን የአውሮፓ ሀገራት ለከፍተኛ ወጪ ዳርጎ ስለነበር ጦርነቱ ብዙም ያልነካት አሜሪካ ከፍተኛ የወርቅ ክምችት ይዛ በመገኘቷ ዶላር በሀገራት መካከል የሚካሄድ ግብይት ማቀላጠፊያ እንዲሆን መወሰኑን የሚያወሱት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፤ ከዚያ በኋላም አሜሪካን አምባገነን እንደሆነች ይጠቅሳሉ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው እንደሚያብራሩት፤ ዶላር የዓለም መገበያያ መሆኑ የራሳቸው ገንዘብ ስለሆነ አሜሪካኖችን ነው የሚጠቅመው። የአሜሪካ መንግሥት ከባንኮች የተበደረው ዕዳ ወደ 33 ትሪሊየን ዶላር ደርሷል። የዋጋ ግሽበት እና የኢኮኖሚ ውድቀት ስለሚያመጣ በአንድ ጊዜ አያደርጉትም እንጂ የተጠቀሰውን የገንዘብ መጠን በኤሌክትሮኒክ አትመው ቢለቁ ከዕዳ ነፃ መሆን ይችላሉ። ሌሎች ሀገራት ግን ዕዳ ካለባቸው ዶላር ፈልገው ነው መክፈል ያለባቸው። ስለዚህ ከዚህ ጫና ለመላቀቅ ነው ሀገራት በራሳቸው ገንዘብ ለመገበያየት ስምምነቶችን እየተፈራረሙ ይገኛሉ።
በዓለም የንግድ ሥርዓት እስከ 80 በመቶ የገንዘብ ልውውጥ የሚደረገው በአሜሪካን ዶላር ነው። ሀገሮች ገንዘባቸውን ወደ ዶላር ለመቀየር ከፍተኛ ኮሚሽን ይከፍላሉ የሚሉት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፤ አሜሪካ በተለያዩ ሀገራት ላይ ማዕቀብ በመጣል ገንዘብ እንዳያንቀሳቅሱ ታደርጋለች። ሀገራት ይሄን ማዕቀብ ለመሸሽ ሲሉም በራሳቸው ገንዘብ መገበያየት ይፈልጋሉ። የዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ ሩሲያን ከአውሮፓውያኑ የገንዘብ ማስተላለፊያ ስዊፍት ካወጧት በኋላ በራሳችን ገንዘብ እንገበያይ የሚለው ሀሳብ እየጎለበተ መምጣቱን ያስረዳሉ።
አያይዘውም፤ እንደ አሜሪካን ያሉ ሀገራት ከተፎካካሪዎቻቸው ጋር መፋጠጥ ውስጥ ሲገቡ ከጦርነት ባሻገር የሚያደርጉት ነገር ማዕቀብ መጣል ነው። አሜሪካ በኢራን እና ሩሲያ ላይ የምትጥለው ማዕቀብ እየጎዳ ያለው ሁለቱን ሀገሮች ብቻ ሳይሆን ከእነሱ ጋር የንግድ ልውውጥ የሚያደርጉ ሀገራትን ጭምር ነው። ይሄ ማለት በአንድ ሀገር ላይ የሚጣል ማዕቀብ በርካታ ሀገራትን ሥራ እንዳይሠሩ የማድረግ አቅም አለው ማለት ነው። የሚጥሉትን ማዕቀብ የሚያስፈጽሙበት ትልቁ ችሎታቸው የአሜሪካን ዶላርን እንዳይጠቀሙ መከልከል ነው። በራስ ገንዘብ መገበያየት ይህንን ማዕቀብ ጉልበት አልባ ያደርገዋል ብለዋል።
በተለይም የብሪክስ አባል ሀገራት በራሳቸው ገንዘብ ለመገበያየት ስምምነት እያደረጉ ያሉት የአሜሪካንን አምባገነንነት ለመገዳደር ነው። ሩሲያ ለቻይና የምትሸጠውን ነዳጅ ክፍያ በዩሃን ነው የምትቀበለው፣ ይህን ገንዘብ ከቻይና ለምታስገባቸው የተለያዩ ሸቀጦች ግዢ ትጠቀመዋለች። ይህ የአሜሪካንን ዶላር ከጫወታ ውጭ የሚያደርግ አካሄድ ነው። የብሪክስ ሀገራት ዋነኛ ግብ ሁሉም ሀገራት በሉዓላዊነት ተሳትፎ ኖሯቸው ዓለም በእኩልነት የምትተዳደርበትን ሁኔታ መፍጠር ነው ሲሉም ያክላሉ።
ኢትዮጵያ በራስ ገንዘብ ለመገበያየት ከሀገራት ጋር የምታደርገው ስምምነት የሚኖረውን ፋይዳ ሲያስረዱም፤ አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ክፍተት አለ። ከሀገራት ጋር በራስ ገንዘብ መገበያየት የሚያስችል ስምምነት መፈረሙ ክፍተቱን ለመሸፈን ይረዳል ብለዋል።
የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተለያየ ጊዜ የሰጧቸው መግለጫዎች እና አስተያየቶች እንደሚያመለክቱት ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር በራስ ገንዘብ ለመገበያየት ስምምነቶች መፈራረሟ በርካታ ጠቀሜታዎች የሚያስገኝ ነው።
ኢትዮጵያ እና ቻይና ብር እና ዩሃን በመጠቀም ያለ ዶላር በመካከላቸው ግብይት እና ኢንቨስትመንት ለማካሄድ ስምምነት በመፈረሙበት ወቅት የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ ባደረጉት ንግግር የስምምነቱ ግቡ የንግድ ልውውጥን ማሳደግ፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን መቅረፍ እና በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ማጠናከር ነው ብለዋል።
በተመሳሳይ መንገድ ኢትዮጵያ እና የተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶች ለግብይት የራሳቸውን ገንዘብ ለመጠቀም ሲስማሙ፣ ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱ በሰጡት አስተያየት፤ ሁለቱ ሀገራት በራሳቸው መገበያያ ገንዘብ ለመገበያያት መስማማታቸው ለኢትዮጵያ ተጨማሪ ፈንድ እንድታገኝ ያስችላታል። የምንጠቀመውን የወጪ ንግድ መገበያያ ገንዘብ አማራጭ ያሰፋልናል፤ እንዲሁም በመጪዎቹ ዓመታት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያድጋል ተብሎ የሚጠበቀውን የንግድ እና የኢንቨስትመንት ግብይቶች ለማሳለጥ ይረዳናል ብለዋል።
የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኙ ሸዋፈራው ሽታውን በበኩላቸው፤ እ.አ.አ በ1991 ሶቭየት ኅብረት የምትባለዋ ግዙፍ ሀገር በይፋ ፍርክስክሷ ከወጣ በኋላ የዓለም ፖሊስ ሆና የተሰየመችው አሜሪካ ናት። ዓለም በአንድ ጡንቸኛ ሀገር የመመራቷ ነገር እያበቃ ይመስላል። አሁን ብሪክስ የሚባል ስብስብ ወደፊት እየመጣ ነው። የአሜሪካ ወዳጅ የሚባሉ ሀገራትም ቡድኑን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ። ይህ ስብስብ የአሜሪካን ዶላርን ገሸሽ በማድረግ አባላቱ በራሳቸው ገንዘብ እንዲገበያዩ እየሠራ ነው፤ ተሳክቶላቸዋልም ነው የሚሉት።
የቻይና፣ የብራዚል እና የሕንድ ኢኮኖሚ ደግሞ ከማንም በማይተናነስ መልኩ ወደፊት እየመጣ መሆኑን የሚጠቁሙት ሸዋፈራው፤ የብሪክስ ሀገራት ሀብት በጥቅል የአሜሪካንን በልጦ በተገኘ ጊዜ የዓለም ፖለቲካዊ የኢኮኖሚ ሥርዓት አቅጣጫውን እንደሚቀይር የሚያመላክቱ ብዙ ነገሮች አሉ ብለዋል።
የብሪክስ ሀገራት የራሳቸውን ገንዘብ አቅም በማሳደግ ዶላርን ዋጋ ለማሳጣት እየጣሩ ነው የሚሉት የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኙ፤ ወደፊት የኃይል አሰላለፍ ለውጥ መኖሩ አይቀሬ ይመስላል። ኢትዮጵያም ከሚለወጠው ዓለም ጋር ተወዳዳሪ ሆና ለመዝለቅና ድርሻዋን ማግኘት እንድንችል የቤት ሥራዋን ቀድማ ማገባደድ ይኖርባታል ሲሉ አሳስበዋል።
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26 ቀን 2017 ዓ.ም