ሁሉም ሕጎች በራሳቸው ምሉዕ ባለመሆናቸው፣ ሕጎችን በተገቢው የአተረጓጎም ሥርዓት ተርጉሞ ሥራ ላይ ማዋል አስፈላጊ መሆኑን የሕግ ምሑራን ያስረዳሉ። የየሀገሩ የበላይ የሆነው ሕገ መንግሥት ፍጹም ገለልተኛና የሕገ መንግሥትን የመተርጎም ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ባሉት የሕገ መንግሥት ተርጓሚ አካል ሊተረጎም እንደሚገባውም ይታመንበታል። ለዚህም ሀገራት ሕገ መንግሥትን የሚተረጉሙ ተቋማት አሏቸው።
በኢትዮጵያም ሕገ መንግሥትን የመተርጎም ሥልጣን ለኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት የተሰጠ ሥልጣን ነው። ጽሕፈት ቤቱ የቀረበለት አቤቱታ የሕገ መንግሥት ትርጉም የሚያሻው መሆኑን ካረጋገጠና የሕገ መንግሥት መብት ጥሰት ተፈጽሞበታል ብሎ ካመነ የውሳኔ ሐሳቡን
ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀርባል። የፌዴሬሽን ምክር ቤትም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 መሠረት ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን ተሰጠው በመሆኑ ጽሕፈት ቤቱ ያቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ አጣርቶ ውሳኔ ይሰጣል።
ይህ ቢሆንም ግን፣ ከሕገ መንግሥት ትርጉም ጋር የማይገናኙ አቤቱታዎች የአጣሪ ጉባዔውን ጊዜ እና የሰው ኃይል ብሎም በጽሕፈት ቤቱ ሊታዩ የሚገባቸውን የሕገ መንግሥት ትርጉም ጉዳዮች ጊዜ እየተሻሙ እንዳሉ የጉባዔ ጽሕፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ ወዬሳ ይናገራሉ።
ዳይሬክተሩ እንዳስረዱት፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም ምንነትና የሕገ መንግሥት መብት ጥሰት ሲባል ምን ማለት ነው የሚለው ላይ ከፍተኛ የግንዛቤ ክፍተት በመኖሩ ሳቢያ ተቋሙን ከፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት ቀጥሎ ያለ የይግባኝ ፍርድ ቤት አድርጎ የመቁጠር አስተሳሰብ ይስተዋላል። በዚህ ሳቢያ ጉባዔ ጽሕፈት ቤቱ ከሕገ መንግሥት ትርጉም ጋር ተያያዥነት የሌላቸው በርካታ መዝገቦች እየቀረቡለት ይገኛሉ።
ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊነቱ ሕገ መንግሥትን የመተርጎም እንጂ ሕግን የመተርጎም አይደለም ያሉት አቶ ደሳለኝ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 78 መሠረት ሕግን የመተርጎም ሥልጣን ለፍርድ ቤቶች የተሰጠ ነው። ጉባዔው ደግሞ ከተሰጠው ሥልጣን ውጪ የመደበኛ ፍርድ ቤት ሥራን አይሠራም።
በጽሕፈት ቤቱ የጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ ከላሊ ኪሮስ፤ ወደ ጽሕፈት ቤቱ ከሚመጡ መዝገቦች መካከል ከ97 ከመቶ በላይ የሚሆኑት የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም ተብለው የሚመለሱ መሆናቸውን ያነሳሉ።
አቶ ከላሊ እንደሚሉት፤ ሁለት ተከራካሪዎች በፍርድ ቤት ተገቢውን ሂደት አልፈው ማስረጃ አቅርበው ፍርድ ቤቱ አሳማኝ የሆነውን ማስረጃና እና ክርክር ላቀረበው ወገን ከወሰነ በኋላ አንደኛው ወገን ለምን ለእኔ አልተወሰነልኝም በሚል መነሻ ሕገ መንግሥታዊ መብቴ ተጥሷል ብሎ አቤቱታውን ለጽሕፈት ቤቱ ያቀርባል። ይህ ሰው የተከራከረበት ጉዳይ ለምሳሌ የንብረት ጉዳይ ቢሆንና ንብረት የማፍራት መብቴ ተጥሷል ብሎ ቢመጣ ሕገ መንግሥቱ ንብረት የማፍራት መብትን የሰጠው ለሁለቱም ግራና ቀኝ አካላት እንጂ ለአንዱ ብቻ ሊሆን አይችልም፤ ፍርድ ቤቱ የቀረበለትን የይዞታ ማረጋገጫ አሳማኝነት አረጋግጦ ፍርድ ከሰጠ ተገቢ ማስረጃ ላቀረበው አካል ተፈርዶለታል ማለት ነው። የተረታው ተከራካሪ ማስረጃው ትክክል አይደለም ወይም የተጭበረበረ ነው፤ ተገቢ ውሳኔ አይደለም ካለም አሳማኝ መከራከሪያ በመያዝ በይግባኝ ማቅረብና መከራከር ይችላል። እንዲህ ያለው ጉዳይ ሕገ መንግሥታዊ መብቴን ጥሷል በሚል ሊቀርብ የሚችለው አንድ ባለጉዳይ ክስህን ለፍርድ ቤት ማቅረብ አትችልም፣ እንዲህ ያለ ማስረጃ ማቅረብ አትችልም፣ ፍርድ ቤት ቆመህ መከራከር አትችልም ቢባል ነበር፤ ነገር ግን እሱን የሚያስደስት ውሳኔ ስላልተወሰነለት ብቻ ሕገ መንግሥታዊ መብቴ ተጥሷል የሚል አቤቱታ ሕግ መንግሥታዊ ሊሆን አይችልም።
የጽሕፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር፤ የሕገ መንግሥት መብት ጥሰት ከተፈጸመባቸውና የሆኑ የሕገ መንግሥት ትርጉም የውሳኔ ሐሳቡን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀረበባቸውን ጉዳዮች መካከል ሁለቱን ለማሳያነት ይጠቅሳሉ። አንደኛው ለዜጎች የተሰጠውን የዋስትና መብትን የሚቃረን፣ ዜጎች ዋስትና መብታቸው በፍርድ ቤት እንዳይረጋገጥ የሚከለክለው የአደገኛ ቦዘኔ አዋጅ ሲሆን፣ ይህም ዜጎች በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠላቸውን ፍትሕ የማግኘትና ዜጎችን መብት እና ነፃነት የሚጋፋ በመሆኑ፣ ዋስትና መብት መከልከሉ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም በሚል የሕገ መንግሥት ትርጉም ተሰጥቶበታል፡፤፡
ሁለተኛው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ጋር የተያያዘ ሲሆን የዕጣ አወጣጥ መርሐ ግብሩ ክፍያቸውን ሙሉ በሙሉ ያጠናቀቁትን የሚመለከት ነው የሚል ጉዳይ ሲባል ይህ በዜጎች መካከል በሀብት፣ በዘር፣ በሃይማኖት ልዩነት መፍጠር በሕገ መንግሥቱ በግልጽ የተከለከለ በመሆኑና ከዚህም በተጨማሪ ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ልማት ዓላማ ያፈነገጠ አሠራር መሆኑን አረጋግጦ የወጣውን የዕጣ አወጣጥ መመሪያ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው በማለት የውሳኔ ሐሳቡን ለፌደሬሽን ምክር ቤት አቅርቧል።
ጉባዔው ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከቀረቡለትና ከተመለከታቸው ስድስት ሺ 283 መዝገቦች መካከል ትክክለኛ የሕገ መንግሥት መብት ጥሰት የተፈጸመባቸው መዝገቦች 138ቱ መሆናቸውን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ ጉባዔው ጋር መቅረብ የሌለባቸው ጉዳዮች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ያመላክታሉ።
የጽሕፈት ቤቱ ተግባር ምንድነው የሚለው ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖር ለማስቻል በዚህ ዓመት ለጉባዔው የሚቀርቡ አቤቱታዎች ምን ምን መስፈርቶችን ማሟላት አለባቸው? የሕገ መንግሥት ትርጉም ጉዳይ የሆኑት የትኞቹ ናቸው? በሚሉት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንደሚሰጥ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለዳኞች፣ ጠበቆች፣ የፍትሕ አካላትና ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ለመስጠት የታቀደው የግንዛቤ ማስጨበጫ አቤቱታ አቅራቢዎች የሕገ መንግሥት መብት ጥሰትን ብቻ ላይተው ለጉባዔ ጽሕፈት ቤቱ እንዲያቀርቡ ያግዛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ይናገራሉ።
አቶ ከላሊ በበኩላቸው፣ በጉባዔው የውሳኔ ሀሳብ አቅራቢነት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች ለጽ/ቤቱ መቅረብ ያለባቸው ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው ለሚለው ጥሩ አስረጂ መሆናቸውን ገልጸው፣ ነገር ግን ውሳኔዎችን የማሳተምና በበቂ መጠን ተደራሽ አለመሆናቸው አንዱ ክፍተት መሆኑን አንስተዋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች በመጽሔት መልክ በበቂ መጠን ተደራሽ ቢደረግ በሕግ መተርጎምና በሕገ መንግሥት ትርጉም መካከል ያለውን ልዩነት ለመረዳትና ወደ ጽሕፈት ቤቱ መምጣት ያለባቸው አቤቱታዎች ምን አይነት መስፈርትን ሊያሟሉ ይገባል በሚለው ላይ ያለውን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት እንደሚረዳ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዮርዳኖስ ፍቅሩ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26 ቀን 2017 ዓ.ም