የ2024 የዓለም አቀፍ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ዋንጫ አህጉራዊ ቻምፒዮና በኢትዮጵያ እየተካሄደ ይገኛል። ውድድሩ ባለፈው ቅዳሜ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የተጀመረ ሲሆን፣ “ስፖርት ለአህጉራዊ ሰላም” በሚል መሪ ቃል እስከ ጥቅምት 27-2017 ዓ.ም ይቀጥላል።
በውድድሩ መክፈቻ ሥነሥርዓት የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ ልዩ ባህላዊ ቅርስ ባለቤት እንደመሆኗ ስፖርቱም በተመሳሳይ ሁኔታ ረዘም ያለ ታሪክ እንዳለው በማስታወስ፣ በሀገራችን የአትሌቲክስ ስፖርት ፍቅር የተለየ ነው ሲሉ ተናግረዋል። “ስለ አትሌቲክስ ስናነሳ አበበ ቢቂላን አለማስታወስ አይቻልም፣ እሱ ያሳረፈው ዐሻራ በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና አፍሪካውያን የአትሌቲክስ ፍቅር የጫረ ነው” ብለዋል።
ሚኒስትሯ አክለውም፣ የእጅ ኳስ ስፖርት ኢትዮጵያ ውስጥ እያደገና ውጤት እያመጣ ያለ ስፖርት ነው በማለት ፤ ከዚህ የበለጠ ስፖርቱን ለማሳደግ ድጋፍና ክትትል እንደሚፈልግም ገልጸዋል። ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የእጅ ኳስን ጨምሮ ሌሎች ስፖርቶች እንዲስፋፉና ውጤት እንዲያመጡ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እየሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
“የአፍሪካ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ኢትዮጵያ ይህን ውድድር ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ በመምረጣችሁ በኢትዮጵያ መንግሥት ስም ልባዊ ምስጋናየን አቀርባለሁ፣ ከዚህም በተጨማሪ ስፖርቱ በአህጉር አቀፍ ደረጃ እንዲያድግ ድጋፍ እናደርጋለን” ሲሉ ቃል ገብተዋል።
ከውድድሩ በተጨማሪ የዓለም አቀፍ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የአፍሪካ አህጉራዊ ዋንጫ የወጣቶችና ታዳጊዎች ውድድርን ለሚመሩ ደኞች ሥልጠና የሰጡ ሲሆን፣ የምስራቅ አፍሪካ እና የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ፍትህ ወልደሰንበት (ዶ/ር) በሥልጠናው ላይ በመገኘት ለዳኞች እና ለአሰልጣኞች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈው በአጠቃላይ የውድድሩ ዝግጅትን በሚመለከት ገለፃ አድርገዋል፡፡
“የመጣችሁት ወደ አፍሪካ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ነው፤ ውድድሩም በወንድማማቾች መካከል የሚደረግ ነው፤ የውድድሩ አሸናፊዎችም አፍሪካን በመወከል ለዓለም አቀፍ ውድድር የሚያልፉ ስለሆነ በአፍሪካዊነት ማንነትና ስሜት መልካም የሆነ የውድድር ዳኝነት ጊዜ እንደምታሳልፉ ሙሉ እምነት አለኝ” በማለት ገልፀዋል፡፡
አሠልጣኞችና ዳኞችም በበኩላቸው የሚንመራው ትልቅ አህጉራዊ ውድድር እንዲሁም አሸናፊ ሀገራት ለዓለም አቀፍ ውድድር አፍሪካን የሚወከሉ ስለሆነ ውድድሩን በጥብቅ ዲሲፕሊንና በወንድማማችነትና በአብሮነት መንፈስ ለመምራት ዝግጁነታቸውን ገልፀዋል፡፡
በሥልጠናው የዳኞችን ወቅታዊ ብቃት ለመመዘን እና ደረጃውን የጠበቀ የዳኝነት ፕሮፌሽን ለማሳየት የቅድመ ሥልጠና እና የድህረ-ሥልጠና ፈተና እንደሚሰጣቸው አሠልጣኞቻቸው ገልፀዋል፡፡
በውድድሩ የአፍሪካ ከ18 እና 20 ዓመት በታች የወንዶች እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድኖች ተሳታፊ ሲሆኑ፣ ከ10 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ፣ 11 ብሔራዊ ቡድኖች ተፎካካሪ ናቸው።
ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ታዳጊና ወጣት ብሔራዊ ቡድኖች የሚሳተፉበት በዚህ ውድድር 6 ከ 18 ዓመት በታችና 5 ከ20 ዓመት በታች በአጠቃላይ 11 ብሔራዊ ቡድኖች ተወዳዳሪ ሆነዋል። ኢትዮጵያ፣ ማዳጋስካር፣ ጊኒ፣ ካሜሩን፣ ዛምቢያ እና ናይጄሪያ በ18 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖቻቸው ሲወዳደሩ፤ ሪዩኒየን፣ ዚምቧቡዌ፣ ሩዋንዳ፣ ጊኒ እና ኮንጎ በ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖቻቸው ይወዳደራሉ።
በሁለቱም የእድሜ እርከኖች ውድድሩን አንደኛ በመሆን የሚያጠናቅቁ ሁለት ብሔራዊ ቡድኖች አፍሪካን በመወከል በዓለም እጅ ኳስ ዋንጫ እንደሚወዳደሩ ተገልጿል።
ውድድሩ በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት ሲካሄድ የዓለም አቀፍ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ከአፍሪካ እጅ ኳስ ኮንፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ይመራዋል።
ለውድድሩ በአጠቃላይ ከ180 በላይ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ሲሆን፣ አንድ ቡድን 17 ልዑክ እንደሚያካተት ታውቋል። ለአሠልጣኞች ሥልጠና የሚሰጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች ከዓለም አቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን ሲመጡ፣ ውድድሩን የሚቆጣጠሩ ሁለት ባለሙያዎች እና ውድድሩን የሚመሩ አስር ዳኞችም ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ከውድድሩ አስቀድሞ በተሰጠው መግለጫ ተጠቁሞ ነበር።
ከ18 ዓመት በታች ውድድር ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን የዛምቢያ አቻቸውን 41 ለ 14 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በድል ጀምሯል።
በተመሳሳይ በውድድሩ የመጀመሪያ ቀን ውሎ ከ20 ዓመት በታች በተደረገ ፉክክር ሪዩኒየን ዚምባብዌ 36ለ 26 የረታ ሲሆን፣ ከ18 ዓመት በታች ውድድር ደግሞ ጊኒ ካሜሩንን 31 ለ 29 ማሸነፍ ችላለች።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም