በክልሉ የተከሰተውን የወባ በሽታ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡በሲዳማ ክልል ሃዋሳ ከተማን ጨምሮ በሰባት ወረዳዎች የተከሰተውን የወባ በሽታ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር እየተሠራ መሆኑን የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

የሲዳማ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዳመነ ደባልቄ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በክልሉ በሃዋሳ ከተማ እና በሌሎች 6 ወረዳዎች የወባ ወረርሽኝ ተከስቷል፡፡

የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቁመው፤ የወባ በሽታ ያለባቸውን ሰዎች ልየታ በማድረግ እና ወደ ጤና ተቋም እንዲሄዱ በማድረግ አስፈላጊውን ሕክምና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በህክምና ተቋማትም አስፈላጊውን ግብዓት በማሟላት ታካሚዎች ጥሩ ህክምና እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡ በክልሉ ባለፈው ዓመት የተሰራጨ አጎበር መኖሩን አስታውሰው ያለውን አጎበር በአግባቡ እንዲጠቀሙ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በየወረዳው የአካባቢ ንጽህና እንዲጠበቅ የማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አመላክተው በተለይ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በማፋሰስ እና በማዳፈን ከፍተኛ የሆነ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በባለፈው በጀት ዓመት በክልሉ 915 ሺህ አጎበሮች መሰራጨታቸውን ተናግረው፤ በተያዘው በጀት ዓመትም ተጨማሪ አጎበሮች ለማሰራጨት ለጤና ሚኒስቴር ጥያቄ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡

የመከላከያ ኬሚካል በሀገር ውስጥ መመረት በመቆሙ ምክንያት እጥረት መኖሩን ገልጸው በአራት ወረዳዎች ላይ ርጭት ተደርጓል ብለዋል፡፡

ተጨማሪ ኬሚካል እንዲላክም ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ጥያቄ መቅረቡን አክለው ገልጸዋል፡፡

በአራት ወረዳዎች በተደረገ የኬሚካል ርጭት ከ400 ሺ በላይ ነዋሪዎችን ከወባ በሽታ የመከላከል ሥራ መሠራቱን የጠቆሙት ዋና ዳሬክተሩ፤ በየአከባቢው ሕብረተሰቡ ስለወባ በሽታ ግንዛቤ እንዲኖረው በተለይ የሀገር ሽማግሌዎችን እና የሃይማኖት አባቶችን በመጠቀም ትምህርት እየተሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ ክልሉ በሽታውን በመቆጣጠር የተሻለ አፈጻጸም እንዳለው ተናግረው የቁጥጥር ሥራ በሚገባ በመሰራቱ በክልሉ በአራት ወራት ውስጥ በበሽታው ምክንያት ያጋጠመው የሞት መጠን አንድ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የበሽታው ስርጭት እስከ ህዳር ወር መጨረሻ ሊቆይ እንደሚችል ተናግረው የቁጥጥር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል፡፡

የወባ በሽታ በወባ ትንኝ ንክሻ የሚተላለፍ በመሆኑ ሕብረተሰቡ አጎበርን በመጠቀም፣ ጉድጓዶች ካሉ በመድፈን፣ የወባ በሽታ ምልክት ያለበትን ሰው በአስቸኳይ ወደ ህክምና ማዕከል ሄዶ እንዲታከም በማድረግ በሽታውን እንዲከላከል ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You