በክልሉ ከ60 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል

አዲስ አበባ፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዘንድሮ ዓመት 769 ሺህ 724 ሄክታር መሬት በማልማት ከ60 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለማሪያም ተስፋዬ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በክልሉ በዘንድሮ ዓመት ከ29 ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ከመኸር ወቅት ዓመታዊ ሰብሎች፤ ከ22 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ከፍራፍሬ ሰብሎች እና ከስምንት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ከእንሰት ሰብል ይመረታል።

በድምሩ 769 ሺህ 724 ሄክታር መሬት በማልማት 60 ሚሊዮን 094 ሺህ 261 ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቀዶ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም የ15 በመቶ የምርት እድገት ይጠበቃል ያሉት አቶ ኃይለማሪያም፤ በዓመታዊ አዝዕርትና ሆርቲካልቸር ሰብሎች 715 ሺህ 945 ሄክታር ማሳ እንደለማ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በአትክልትና ፍራፍሬ ዓመታዊ ሰብሎች 87 ሺህ 640 ሄክታር የለማ ሲሆን 22 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡ ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 16 በመቶ እድገት እንዳለው አስረድተዋል። እስካሁን 15 ሺህ 855 ሄክታር የማሳ ላይ ምርት መሰብሰቡን ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ በበልግ ወቅት ከለማ የሆርቲካልቸር ዓመታዊ ሰብሎች 150 ሺህ 773 ሄክታር ማሳ ላይ ከ38 ነጥብ አምሥት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተገኝቷል ያሉት አቶ ኃይለማሪያም፤ የግብርና ዘርፍ በክልሉ ኢኮኖሚ እድገትና ድህነትን በመቀነስ ረገድ ባለው ወሳኝ ድርሻ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል።

ዘርፉ የሚጠበቅበትን ውጤት ለማሳካት የተነደፉ ሀገራዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ለማሳካት በየወቅቱ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ገልጸው፤ በዚህም የውሃ ሀብታችን በላቀ ደረጃ በመጠቀም የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል ጥረት መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ግብርና በምግብ እራስን ከመቻል አልፎ ለገበያ የሚሆን ምርት ማምረት እንዲችል በመስኖ የማልማት፣ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም፣ ምርጥ ተሞክሮዎችን ወደ ሁሉም አርሶ አደሮች የማዳረስ ሥራ እንደተሠራ ተናግረዋል።

እንደ አቶ ኃይለማያርም ገለፃ፤ የኩታ ገጠም እርሻን እንዲተገበር በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል። የሌማት ትሩፋት የአረንጓዴ ዐሻራና የበጋ ስንዴ ልማት ተሞክሮን በመከተል የተቀናጀ ክልላዊ የወተት፣ ዶሮ፣ የማር እና ስጋ ምርት ማሻሻያ ፕሮግራም በመዘርጋት ምግብና ሥርዓት ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ተሠርቷል።

ሀገራዊ የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም ጋር በማቀናጀት የእንስሳት ሀብት ልማትን ከፍራፍሬ ሰብሎች ጋር በማስተሳሰር እየተሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You