አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ክልል ከስድስት ሺህ 300 በላይ ቀበሌዎች ውስጥ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ተቋቁመው በሥራ ላይ መሆናቸውን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ጋዛሊ አባሲመል ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በክልሉ ከተወሰኑ ቀበሌዎች ውጪ በአብዛኛው ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ተቋቁመው በሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከስድስት ሺህ 300 በላይ ቀበሌዎች ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ተቋቁመዋል፡፡
የባህላዊ ፍርድ ቤቶቹ መቋቋም የመደበኛውን ፍርድ ቤት ጫና እየቀነሰ እና የሕዝቡ በአቅራቢያው ፍትህን እንዲያገኝ እያስቻለ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሕዝብ ዘንድ ያለው ቅቡልነትም እያደገ መሆኑን
ፕሬዚዳንቱ፤ የኦሮሚያ ባህላዊ ፍርድ ቤት ከመቋቋሙ በፊት አስፈላጊነቱ ላይ ጥናት መደረጉን አንስተዋል፡፡
ወደ መደበኛው ፍርድ ቤት የሚመጡ ጉዳዮች በየጊዜው እየጨመሩ እንደሆነ እና የፍትህ መረጋገጥ ላይ የተለያዩ ማነቆዎች ይታዩ እንደነበር አመላክተው፤ ይህንን ለማቅረፍ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ባህላዊ ፍርድ ቤቱ መቋቋም እንዳለበት ታምኖ በጨፌ እንዲጸድቅ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡ ደንብ ወጥቶለት ወደ ሥራ መግባቱንም ገልጸዋል፡፡
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ ወደ ሥራ ሲገባ ባህላዊ ፍርድ ቤትን ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን ህብረተሰቡ ተረድቶ እንዲጠቀምበት በባህላዊ ፍርድ ቤቱ ውስጥ የሚሠሩና መስፈርቱን የሚያሟሉ ሽማግሌዎችን የመምረጥ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ በዚህም ባህላዊ ፍርድ ቤቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በመጀመሪያው ዓመት 50 ሺህ ፋይሎች፤ በሁለተኛው ዓመት 150 ሺህ ፋይሎች እንዲሁም ባሳለፍነው ዓመት 486 ሺህ ጉዳዮች ወደ ባህላዊ ፍርድ ቤት መጥተዋል።
ባህላዊ ፍርድ ቤት ከመቋቋሙ በፊት ለመደበኛው ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ጉዳዮች ከ15 በመቶ እስከ 20 በመቶ እየጨመረ እንደነበር አንስተው፤ ፍርድ ቤቶቹ ከተቋቋመ በኋላ ለመደበኛ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ጉዳዮች እየቀነሱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ይህንን ተሞክሮ ለሁሉም ክልሎች ማጋራት እንደተቻለም ጠቁመዋል፡፡
ሕዝቡ ባህላዊ ፍርድ ቤቱን በአግባቡ እየተጠቀመበት መሆኑን ከሚቀርቡት ጉዳዮች ማወቅ ይቻላል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በተደረገ ጥናትም 92 በመቶ ያህል በሕዝብ ዘንድ ቅቡልነትን ማግኘት እንደቻለ ገልጸዋል፡፡ ይህ ህብረተሰቡ ፍትህን ባለበት ቦታ ሆኖ እንዲያገኝ አስተዋጽኦ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ባህላዊ ፍርድ ቤቶቹ ጉዳዮችን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት በመውሰድ የሚጠፋውን ጊዜና ወጪ መቆጠብ የቻሉ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም