አስር አዳዲስ የአየር ብክለት መለኪያ መሣሪያዎች ሊተከሉ ነው

አዲስ አበባ፡- በመዲናዋ አሥር ለአየር ብክለት መለኪያ አገልግሎት የሚውሉ አዳዲስ መሣሪያዎች ሊተከሉ መሆኑን የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የአማቂ ጋዝ ልኬት፣ ቅነሳና አረንጓዴ ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ቡድን መሪ አቶ ሰለሞን መለሰ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ የከተማዋን የአየር ብክለት ምጣኔ ለማወቅና ለመቀነስ የሚረዱ ርምጃዎች ለመውሰድ አሥር አዳዲስ የአየር ብክለት መለኪያ መሣሪያዎች ይተከላሉ፡፡

ከዚህ በፊት በከተማው የአየር ብክለት መለካት የሚችሉ ዘጠኝ ማሽኖች ተተክለው እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሰለሞን፤ ማሽኖቹ የታሰበውን ያህል ውጤታማ ባለመሆናቸው በምትካቸው አሥር አዳዲስ የአየር ብክለት መለኪያ መሣሪያዎች ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አሁን አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ማሽኖች ዘመናዊ ባለመሆናቸው ተገቢውን ምላሽ እየሰጡ የሚገኙት ከዘጠኝ ማሽኖች መካከል ሦስቱ ብቻ መሆናቸውንም ነው አቶ ሰለሞን የጠቆሙት፡፡

አቶ ሰለሞን አክለውም፤ ባለሥልጣኑ ካስተከላቸው ውጪ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ የተከሏቸው ማሽኖች ለዚሁ ዓላማ እየዋሉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

መሣሪያዎቹም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ በጃክሮስ፣ በአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ጊቢ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ እና ስድስት ኪሎ እንዲሁም በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ጊቢ ውስጥ ይገኛሉ ያሉ ሲሆን፣ መሣሪያዎቹ ለአተነፋፈስ ችግር የሚሆኑ ደቃቅ ንጥረ ነገሮችን የሚለኩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

መለኪያ መሣሪያዎቹ ባለፈው ዓመት ለመተካት ታቅዶ ወጪው ከፍተኛ በመሆኑ ለዚህኛው በጀት ዓመት እንዲዘዋወር መደረጉን ጠቅሰው፤ በቅርቡ ጨረታ ወጥቶ ወደ ግዢ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ፤ የመሣሪያዎቹ መተከል የከተማውን የአየር ብክለት አሳሳቢነት በመረዳት ተገቢውን ርምጃ ለመውሰድ ያግዛል፡፡ ከዚህ በፊት የተተከሉት ማሽኖች በሚፈለገው ልክ ውጤት ባያስገኙም በከተማው የአየር ብክለት መጨመሩ ጥቆማዎችን በመስጠት በዋናነት የአሮጌ መኪኖች መመሪያ እንዲዘጋጅ አስችሏል፡፡

መሣሪያዎቹን በተያዘው በጀት ዓመት ተክሎ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዟል ያሉት አቶ ሰለሞን፤ መሣሪያዎቹን ለመትከል በመንግሥት የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ በመሆኑ ሰፊ በጀት እንደተያዘ አብራርተዋል፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You