ከቱሪዝም ዘርፍ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት ሰላም ላይ መሥራት ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፡- ከቱሪዝም ዘርፍ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት ብሎም ዘርፉን ሙሉ ለማድረግ ሰላም ላይ መሥራት ያስፈልጋል ሲል የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ፡፡

በዓለም 45ኛ፣ በኢትዮጵያ ለ37ኛ ጊዜ የዓለም የቱሪዝም ቀንን ምክንያት በማድረግ “ቱሪዝም ለሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ ትኩረቱን በአዲስ አበባ የቱሪዝም ሳምንት ላይ ያደረገ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ከቱሪዝም ዘርፍ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት ብሎም ዘርፉን ሙሉ ለማድረግ ሰላም ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ሰላም የቱሪዝም ፓስፖርት ነው፤ ቱሪዝምም የሰላም ምንጭ ነው ያሉት ዶክተር ሂሩት፤ 80 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ቱሪዝም በባህል፣ ወግና ልማድ እንዲሁም ከእምነት ላይ የሚቀዳ በመሆኑ ቱሪዝም ሰላምን ለማምጣት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዶክተር ሂሩት አክለውም የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሰላምን የማምጣት ኃይሉ ከፍተኛ የሚሆነው አብዛኛው ከባህል የሚቀዳ በመሆኑ ነው ያሉ ሲሆን ባህሎችም ለተለያዩ ችግሮች መፍቻ ቁልፍ ናቸው ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ኃፍታይ ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው፤ በተፈጥሮ ሰላምና ቱሪዝም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ያሉ ሲሆን አንዳቸው ለአንዳቸው ተደጋግፈው ውጤት የሚያስገኙ ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ኃፍታይ ገለጻ፤ ዓለም ላይ እየተስተዋሉ ያሉ የሰላም እጦቶችን ሃይ ለማለት ቱሪዝምን እንደ መሣሪያ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ቱሪዝም ሰዎች እርስ በራሳቸው ከተዋወቁና አንዱ የሌላውን ወግ፣ ልማድ፣ ባህል፣ እሴትና እምነት መረዳት ከቻለ እውቀትን ከመሸመት በተጨማሪ አንድነት የሚያጸናበትም ነው፡፡

ጎብኚዎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌሎች ቦታዎች ሲሄዱ የሚጎበኙትን ህብረተሰብ ባህል፣ ወግ፣ ልማድ፣ አስተሳሰብና እሴት የሚገነዘቡበት እንዲሁም ጥርጣሬዎች እንዲያስወግዱ እድል ስለሚፈጥር ቱሪዝም ለሰላም ቁልፍ ነገር ነው ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሀገር ልማት ጥናት ኮሌጅ የቱሪዝም ልማትና አስተዳደር ረዳት ፕሮፌሰር ኤፍሬም አሰፋ ናቸው፡፡

ሀገራት የነበሩባቸው ችግሮችና መጥፎ ጠባሳዎችን ወደ ሙዚየም በማምጣት ለማስተማሪያነት እንዲሁም ለሰላም መጠቀሚያነት እንዲውሉ ማድረግ እንደቻሉም አስረድተዋል፡፡

በዕለቱም ‹‹ቱሪዝም ለሰላም ሰላም ለቱሪዝም›› በሚል ርዕስ የመነሻ ጽሑፍ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You