የሰነድ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ

በቅርቡ ኢትዮ ቴሌኮም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ለኢትዮጵያውያን የአክሲዮን ሽያጭን ይፋ አድርጓል፡፡ ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ ሥራውን በሚቀጥለው ወር እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡

የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው አካል የሆነው የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ነዋይ ገበያ በካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248/2013 መሠረት በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ትብብር በአክሲዮን ኩባንያነትና በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንደሚቋቋም ተደንግጓል።

ለመሆኑ በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል የተባለው የሰነድ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ ምንድን ነው? በምን መልኩ  ተግባራዊ ይደረጋል ጥቅሞቹስ?

የምጣኔ ሀብት ባለሙያና የፓን አፍሪካ ንግድ ምክር ቤት ኃላፊ አቶ ክቡር ገና፤ ሰነደ ሙዓለ ነዋይ የአክሲዮን ባለቤትነትን፣ በአንድ ድርጅት ውስጥ ያለን የአክሲዮን ልክና መጠን፤ የድርጅቱ ባለቤት ማንነት የሚያሳይና የሚያረጋግጥ ሰነድ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህ መንገድም በዓመቱ መጨረሻ ላይ ትርፍ ከተገኘ ለባለአክሲዮኖች ይከፋፈላል ይላሉ፡፡

አንድ አክሲዮን ገዢ ከመግዛቱ በፊት አክሲዮኑን ስለሚገዛው ድርጅት ማወቅ እንደሚጠበቅበት በመግለጽ፣ ድርጅቱ ከተቋቋመ ስንት ጊዜ እንደሆነው፣ ትርፍ ማምጣት ስለመቻሉ፣ የትርፍ መጠኑ እያደገ መምጣቱን፣ ከተመሳሳይ ድርጅቶች የተሻለ አስተዳደር፣ አገልግሎትና ቅልጥፍና እንዳለው፣ እዳውንም ማወቅ እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡

አክሲዮን ሻጮች የሚያወጧቸው የደንበኛ ሳቢ መግለጫ የድርጅቱ አስተዳደር ያለውን ልምድ፣ ክስ፣ ለአደጋ የማያጋልጥ መሆኑን፣ የዓመት ገቢውን፣ ትርፉን እንደሚያብራራ ጠቅሰው፤ አማካሪዎች ኢንቨስተሮች ስለሚገዟቸው ሰነድ ሙዓለ ነዋይ ጥቅምና ጉዳቱን እንደሚያስረዱም ይገልጻሉ፡፡

የአክሲዮን ገበያ ሁለት ገበያዎች አሉት የሚሉት ባለሙያው፤ አክሲዮን የሚገዙ ሰዎች ወይም ድርጅቶች በመጀመሪያው ገበያ ላይ አክሲዮን ለሽያጭ ሲወጣ እንደሚገዙ በመግለጽ፣ በሁለተኛው ገበያ ደግሞ የገዙትን አክሲዮን ሙሉ በሙሉም ባይሆንም በተወሰነ መልኩ ለገበያ ያቀርቡታል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

በሂደቱ አክሲዮኑን በመጀመሪያው ገበያ ከገዙበት ዋጋ በላይ ማግኘት አለማግኘታቸውን እንደሚያጣሩ  ጠቅሰው፤ ዋጋውን ከፍ ብሎ ካገኙት አክሲዮናቸውን ሊሸጡት የሚችሉ ሲሆን ዝቅ ካለና ገንዘቡ ካላስፈለጋቸው ደግሞ ገበያ አለማውጣት እንደሚችሉም ይገልጻሉ፡፡

የሁለተኛ ዙር ሽያጭ መጀመሪያ ለሸጠው ድርጅት የሚደርሰው ነገር እንደሌለ ጠቅሰው፤ ነገር ግን በመጀመሪያው ዙር አክሲዮኖችን የሸጠው ድርጅት ያልሸጣቸውን በእጁ ላይ የሚገኙ አክሲዮኖችን ለገበያው ሊያቀርብ ይችላል ሲሉ ይናገራሉ፡፡

ከግብይይቱ መንግሥት ሊወስድ የሚችለው ክፍያ ይኖራል የሚሉት ባለሙያው፤ የተወሰነ ግብር፣ ቫት ሊያስከፍል እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡

የሰነደ ሙዓለ ነዋይ ገበያው ባለንብረትና ንብረት የሚፈልጉ የሚሻሻጡበት መሆኑን ጠቅሰው፤ በተዘዋዋሪ መንገድ ካልሆነ በቀር ቀሪው ሕዝብ ጋር የሚደርስ ነገር እንደሌለና ዋና ተጠቃሚው እጁ ላይ አክሲዮንና ገንዘብ ያለው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

አክሲዮን ልክ እንደቋሚ ንብረት ቤትና መሬት የሚታይ መሆኑን በመግለጽ፤ ዋጋቸው አሁን ላይ ወደ ላይ ማደጉ የቀነሰ ቢሆንም በየጊዜው ከፍ ብሎ የሚሄድ መሆኑንና የአክሲዮን ዋጋም በዚህ መልኩ እያደገ ይሄዳል ተብሎ ይታሰባል ይላሉ፡፡

በተወሰነ መልኩ አትራፊነታቸው እየታወቀ ያሉ ትልልቅ ድርጅቶች የዋጋ ንረት ሂሳብ ውስጥ አይገቡም የሚሉት ባለሙያው፤ ነገር ግን ሀገሪቷ ላይ ያለውን የዋጋ ንረት ከፍ ብሎ እንዲሰማ የሚያደርጉና በአሃዝ ያልገቡ ዋና የዋጋ ንረት አምጪዎች መሆናቸውንም ያስረዳሉ፡፡

ሰነድ ሙዓለ ነዋይ በውስጡ አክሲዮን፣ የዕዳ ሰነዶች (ቦንዶች)፣ የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ፣ ከመንግሥት የሚወጣ ቦንድ፣ ኩባንያዎች የሚያወጧቸው የእዳ ሰነዶች (ቦንዶች) በአንድ ላይ ሰብስቦ የያዘ ነው የሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ሥራ አስፈጻሚ ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ዛሬ ላይ 400 ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን የባንኮች እና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች አክሲዮን አላቸው ያሉት ጥላሁን (ዶ/ር)፤ በማህበራዊ ሚዲያ ዋጋ እያዩ፣ ዋና በባንኩ መስሪያ ቤት፣ ገዢና ሻጭ ተገናኝተው፣ ገንዘብ በባንክ በማስተላለፍ፣ ከሰነድ ሙዓለ ነዋዮች ላይ ስማቸው እየተፋቁና መዝገብ እየተቀየረ ሲገበያዩ መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡

ሰዎች አክሲዮናቸውን ሸጠው ገንዘቡን መጠቀም ቢፈልጉ መገበያያ ቦታና መድረክ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ቀደም ሲል ባሉት ጊዜት ገበያ ባለመኖሩ ምክንያት አክሲዮኖችን አዲስ አበባ ላይ ያሉ ሰዎች ብቻ እንዲገዙ ማድረጉን ያስረዳሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ግብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከየትም ቦታ ሆኖ ባለው አቅም እንዲቆጥብበት ማድረግ መሆኑን በመግለጽ፤ ሰዎች የገዙትን አክሲዮች መሸጥ ቢፈልጉ፣ ወደ ፊት ለልጆች ማስተማሪያ አድርገው ውርስ የሚያደርጉበት መቆጠቢያ መንገድ ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡

ሰዎች የመንግሥት እና የግል ተቋማትን አትራፊና አዋጭነታቸውን በማየት፣ የትርፍ ድርሻቸውን በመመርመር አክሲዮችን እና ቦንድ ይገዛሉ ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ በፈለጉ ጊዜ እነዚህን ሰነደ ሙዓሎችን፣ ኩባንያዎችን የሚለዋወጡበትና የሚገበያዩበት መንገድ የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ነዋይ ገበያ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ገበያው ሻጭና ገዢ ለማገናኘት፣ ዋጋ ለማወቅ፣ መረጃ በማቅረብ የዜጎችን ወጪና ጊዜን እንድሚቆጥብ ጠቅሰው፤ የግብይቱ ተሳታፊዎች በአንድ ቦታ በአካል መገናኘት ሳያስፈልጋቸው ግብይቶችን በኤሌክትሮኒክ እንዲፈጽሙ የሚያስችል ሥርዓት እንደሚዘረጋም ይናገራሉ፡፡

ኢትዮ ቴሌኮምን አክሲዮን በመግዛት ላይ የሚገኙ ሰዎች ወደፊት አክሲዮናቸውን መሸጥ መለወጥ ከፈለጉ መሸጫና መለወጫ መድረኩ የኢትዮጵያ የሰነድ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ ነው ሲሉም ያስገነዝባሉ፡፡

በሰነድ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ አባል ለመሆን የአባልነት ምዝገባና ሰርተፍኬት እንደሚያስፈልግ በመግለጽ፤ ለሌሎች አገበያይ ኢንቨስተሮች የውስጥ ደንቦችን፣ በማሠልጠን፣ በማስተማርና በመፈተን አስፈላጊውን መስፈርት ሲያሟሉ ፈቃድ እንደሚሰጣቸውም ያስረዳሉ፡፡

ለሕዝብ አክሲዮን፣ ሰነድ ሙዓለ ነዋዮችን የሚሸጡ ድርጅቶች መጀመሪያ ደንበኛ ሳቢ መግለጫ ማዘጋጀት፤ በካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ማስመዝገብ፤ ኢንቨስትመንት አማካሪ ከቀጠሩ በኋላ ለሕዝብ ማስታወቂያ ማውጣት እንደሚችሉ ይገልጻሉ፡፡

ሰዎች አክሲዮን ከመግዛታቸው በፊት ሰፋ ያሉ ደንበኛ ሳቢ መግለጫን መረዳት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ኢንቨስተሮች ከአማካሪዎቻቸው ጋር ሆነው ደንበኛ ሳቢ መግለጫውን አንብበው የራሳቸውን ግምገማ አድርገው የመወሰን ኃላፊነት በእጃቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡

አገናኝ አባላት ደላሎች በካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ፍቃድ አግኝተው ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ አባል መሆን አለባቸው የሚሉት ጥላሁን (ዶ/ር)፤ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን መገበያየት የሚቻለው አገናኝ አባላት ደላሎች ሲኖሩ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ በተቻለ ፍጥነት ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መሆኑን በመገልጽ፤ የግብዓቶች ግዢ በመፈጸም የቴክኖሎጂ ሙከራ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምርም ይናገራሉ፡፡

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You