በክልሉ ከ2 ሚሊዮን በላይ ሄክታር መሬት በአሲዳማነት ተጠቅቷል
አዲስ አበባ፡- በዘንድሮው ዓመት የአፈር አሲዳማነትን ለማከም ከ400 ሺህ ኩንታል በላይ ኖራ ለማሰራጨት እየተሠራ መሆኑን የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡ በክልሉ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በአሲዳማነት የተጠቃ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የተፈጥሮ ሀብትና የምግብ ዋስትና ኃላፊ አቶ ኤሊያስ ከድር እንደገለጹት፤ የጉደር ኖራ ፋብሪካን የማምረት አቅም በእጥፍ በመጨመር በተያዘው ዓመት ከ400 ሺህ ኩንታል በላይ ኖራ ለማምረት እየተሠራ ነው፡፡
በኦሮሚያ ክልል ከሚታረሰው መሬት ውስጥ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በአፈር አሲዳማነት ተጠቅቷል ያሉት አቶ ኤሊያስ፤ በአሲዳማነት የተጠቃውን መሬት በኖራ ለማከም በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ 527 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ የጉደር ኖራ ፋብሪካ መገንባቱንና ግብዓት የማሟላት ሥራ መሠራቱን ጠቅሰው፤ 2015 ዓ.ም 53 ሺህ ኩንታል ኖራ፣ በ2016 ዓ.ም 191 ሺህ ኩንታል ኖራ መሰራጨቱን አብራርተዋል፡፡ በዘንድሮው ዓመት የፋብሪካውን የማምረት አቅም በእጥፍ በመጨመር ከ400 ሺህ በላይ ኩንታል ኖራ ለማሰራጨት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት የተመረተው 191 ሺህ ኩንታል ኖራ በዩኒየኖችና ማህበራት በኩል የመሬት አሲዳማነት ችግር ወዳለባቸው አካባቢዎች መሠራጨቱን በመግለጽ፤ ዘንድሮ ከባለፈው ዓመት በእጥፍ ለማምረት እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በክልሉ በአፈር አሲዳማነት የተጠቁ መሬቶችን በማከም ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ ኖራን በስፋት በማምረት በአቅራቢዎች በኩል አርሶ አደሩ የሚፈልገውን ያክል እንዲወስድ የብድር አሠራር መዘርጋቱን ነው የተናገሩት፡፡
በክልሉ ያለውን የመሬት አሲዳማነት ለመቅረፍ የልየታና ችግሩ የደረሰበትን ደረጃ በ15 ዞኖች 157 ወረዳ የመለየት ሥራ መሠራቱን ጠቅሰው፤ ከሚታረሰው መሬት 43 በመቶ በአፈር አሲዳማነት መጠቃቱን ገልጸዋል፡፡
በሚቀጥሉት ዓመታት በአሲዳማነት የተጠቃውን መሬት በማከም ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
የጉደር ኖራ ፋብሪካ ለ120 የአካባቢው ዜጎች ቋሚና ጊዜዊ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን በመግለጽ፤ ፋብሪካው በቀን እስከ አንድ ሺህ 800 ኩንታል ኖራ በማምረት ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም