ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ባስከበረ መልኩ የተለያዩ ተቋማት ውስጥ የመግባት ፍላጎት እንዳላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ከሕዝብ እንደራሴዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት አመላክተዋል። ባለ ብዙ ወገን ተቋማትን መቀላቀል ብቻ ሳይሆን ከአረብ ሀገራት ጋር ያለውን ዝምድና በደንብ መመርመርና ጠንካራ ወዳጅነት መፍጠር ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዙሪያዋ ካሉት አካባቢያዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ጋር በአባልነት ብትሥራ ምን ትጠቀማለች በሚለው ጉዳይ ላይም የዘርፉ ባለሙያዎች ምልከታ አላቸው፡፡
በዓባይ ጉዳይ ሞጋችና የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ እንዳስረዱት፤ ዓለም አቀፍ ተሰሚነትን ለመጨመርና አዎንታዊ ተጽዕኖ ለመፍጠር አንዱ ስልታዊ መንገድ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን መቀላቀል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተቋማትን እየተቀላቀለች ትገኛለች፡፡ ይህም ቦታዋን ከፍ ለማድረግ አወንታዊ ውጤት እያመጣ ይገኛል፡፡
ኡስታዝ ካሚል፤ ኢትዮጵያ የተሰሚነት ሚናዋን ለመጨመር እንደ አረብ ሊግ ካሉ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር ህብረትን ብትፈጥር በተለይም እንደ ዓባይ ግድብ ያሉ ጉዳዮችን በሚመለከት የጋራ መግባባትን ሊያሳድግላት ይቻላል ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያን ጂኦፖለቲካዊ ጥቅም ከሚጋሩ ሀገራት ጋር ትብብርን የመፍጠሩ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ይገልጻሉ፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት፣ የመረዳት ደረጃዎች እየተለዋወጡ መምጣታቸውን የሚናገሩት ኡስታዝ ካሚል፤ በዓባይ ግድብ ዙሪያ በተለይም ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጋር የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ተፅዕኖ ፈጣሪ የአረብ ሀገራትን ባካተተ ድርጅት ውስጥ ውጤታማ መፍትሄ ማግኘት እንደሚቻል ይጠቅሳሉ፡፡ ኢትዮጵያም ወደዚህ አካል ብትገባ ውይይቶችን ለማቀላጠፍ፣ ኢትዮጵያዊ አቋም በቀጥታ እንዲነገር ያግዛታል ነው ያሉት፡፡
በተቃዋሚ አካላት የሚተላለፉ የተሳሳቱ መረጃዎችን ለመከላከልና እውነታን ለማቅረብ እንደሚያስችላትም ነው የሚያስገነዝቡት፡፡
እንዲህ ያሉ መድረኮች የዲፕሎማሲ ፋይዳቸው የጎላ እንደሆነ የሚጠቅሱት ኡስታዝ ካሚል፤ በተለይ ከመካከለኛው ምስራቅ አቻ ሀገራት ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር በቀጣናው የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በቀላሉ መፍታት እንደሚቻል አማላካች ጉዳይ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ ይህ መስተጋብር ኢትዮጵያ ለዘላቂ የውሃ አጠቃቀም እና ቀጣናዊ ልማት ያላትን ሃሳብ በግልፅ ለማስተላለፍ የሚያስችል እንደሆነና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ውጥረቶችን የሚቀንስ እንደሆነም ያብራራሉ፡፡
የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው፤ በዙሪያው ካሉት አህጉራዊ፣ ዓለም አቀፋዊና አካባቢያዊ ድርጅቶች ጋር በአባልነትም ይሁን በተባባሪነት መሥራት ለሀገር ብሄራዊ ጥቅም ትልቅ ፋይዳ አለው ይላሉ፡፡ ንግድን ጨምሮ የተለያዩ መስኮች ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ትርጉም ያለው መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
እንደ አምባሳደር ዲና ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ ለመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ቅርብ ናት፡፡ በዚህ አካባቢ ካሉት ተቋማት ውስጥ አባል ብትሆን ትጠቀማለች፡፡ ምክንያቱም እዚህ ቀጣና አካባቢ ያሉ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር ቅርበት አላቸው፡፡ ይህ እንደየተጨባጭ ሁኔታዎች እየታየ አባል ልትሆን የምትችልበትን ዕድል የመፍጠር ጉዳይ መታየት ይኖርበታል፡፡
አረብ ሊግ አባል ለመሆን መስፈርቶቹ አረብ ሀገራት ውስጥ መገኘት ብቻ አይደለም የሚሉት አምባሳደር ዲና፤ በሊጉ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ እንደ ሶማሊያ፣ ሱዳንና መሰል አረብ ያልሆኑ የአካባቢው ሀገራት መኖራቸውን ያነሳሉ፡፡ በዚህም የአረብ ሊግ አባል ለመሆን የግድ አረብ መሆን ማለት እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአባልነትም ሆነ በታዛቢነት በዚህ ቡድን ውስጥ አባል ብትሆን ጥቅሟን የሚጻረሩ ወገኖችን በቅርበት ለመከታተልና ምላሽ ለመስጠት አመቺ መሆኑን ከኡስታዝ ካሚል ጋር የሚስማማ ሃሳብ ይጠቅሳሉ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን አጀንዳዎችን ለመቅረጽም ምቹ እድል እንደሚፈጥር ይገልፃሉ፡፡
በጥቅሉ ተቀናቃኝ ኃይል ባለበት አካባቢ በቅርበት መገኘት ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰው፤ ተሳትፎው ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር የሚደረግ ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ መካከለኛው ምሥራቅ ላይ ስትከተል የነበረው ፖሊሲ ስህተት ነበር ብለዋል፡፡ በሁሉም መመዘኛ መካከለኛው ምስራቅ ቅርብ፣ ጎረቤት፣ ከፍተኛ ሀብት ያለበትና ኢትዮጵያውያን ተቀጥረው ሥራ የሚሠሩበት እንደሆነ በመጥቀስ፤ ከነሱ ጋር ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር አለብን ብለዋል፡፡
በዚህ ቀጣና ያሉት በባህል፣ ቋንቋ እና አምነት ከኢትዮጵያ ጋር የሚተሳሰሩ መሆናቸውን፤ ለኢትዮጵያ እድገትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
በቀጣናው ባለብዙ ወገን ተቋም ውስጥ መግባት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ከዓረብ ሀገራት ጋር ያላትን ዝምድና በደንብ መመርመርና ጠንካራ ወዳጅነት መፍጠር ያስፈጋታል ነው ያሉት፡፡ “ዓለም ከነሱ ጋር እየተረባረበ እኛ ከዚህ ርቀን ብንኖር ኪሳራ እንጂ ጥቅም የለውም ሲሉም አስረድተዋል።
“እኛ ሳንኖር ስንቀር ምን እንደሚሠራ እየታየ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ብሪክስ ላይ መግባቷ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል፡፡
አባልነቱ በአፍሪካ ቀንድ እና በአረብ ክልል የጋራ መሠረተ ልማት እና የንግድ ፕሮጀክቶችን ሊያፋጥኑ በሚችሉ የባለብዙ ወገን ስምምነቶች፤ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማስተዋወቅ እንደ መስመር ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል ኡስታዝ ካሚል ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሆኖም እንደ አረብ ሊግ ያለ ድርጅትን መቀላቀል ረጅም ሂደት እና ለቀጣናዊ ትብብር ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅ ኡስታዝ ካሚል አንስተዋል። የረዥም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ጠቀሜታዎችን ታሳቢ በማድረግ፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደርስባትን ተጽዕኖ ለመመከት የበለጠ የተዋሃደ ቀጣናዊ አቋምን ማጎልበት እንዳለባትም መክረዋል። በጥቅሉ ወደ እንደዚህ ዓይነት ጥምረቶች መሄድ ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ ያላትን ተጽእኖ ሊያጠናክር እንደሚችልና በተመሳሳይ ጊዜ ውስጣዊ መረጋጋት እና ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬን እንደሚጨምርም አስታውቀዋል፡፡
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም