አዲስ አበባ፡- የዲላ መካከለኛ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመጀመሪያ ጊዜ ያመረተውን 22 ቶን የአቮካዶ ዘይት ለውጭ ገበያ ማቅረቡን አስታወቀ፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጥላሁን ብርሃኑ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳሉት፤ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ በሀገር በቀል አልሚ ድርጅት እየተመራ የተቀናጀ የግብርና ምርት እና የኦፕሬሽን ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡ በፓርኩም 22 ቶን የአቮካዶ ዘይት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ተችሏል፡፡
ኢንዱስትሪ ፓርኩ በአሁኑ ሰዓት በአንድ ሽፍት (ለስምንት ሰዓታት) የሚሠራ ሲሆን፤ለመጀመሪያ ጊዜ ያመረተው የአቮካዶ ዘይት ወደ ጣልያን ሀገር መላኩን ገልፀው፤ ቴክኖሎጂ በማሸጋገርና በሥራ ዕድል ፈጠራ ካለው አስተዋፅኦ ባለፈ የአቮካዶ ዘይት ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሩ በእድገትና ሽግግር ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ አመላካች መሆኑን ጠቁመዋል።
ፓርኩ ወደ አስር የሚጠጉ ምርቶች ቡና፣ ወተት፣ እንቁላል እና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ መሰማራር ለሚፈልጉ አልሚ ባለሀብቶች ክፍት መሆኑን ገልፀው፤ አሁን ላይ ፍላጎት ካሳዩ ባለሀብቶች ጋር የሥራ ስምምነት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም በቡናው ዘርፍ ለመሠማራት ጥያቄ ያቀረበ ባለሀብት በፓርኩ ውስጥ ቦታ ተሰጥቶት ወደ ሥራ መግባቱን አመልክተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮፖሬሽን ሁለቱም ፓርኮች በጌዲዮ ዞን ዲላ ከተማ እና ይርጋጨፌ ላይ እያለማ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ የይርጋጨፌ ቡና ታዋቂ በመሆኑ የማምረት አቅም በማሻሻል ምርትን ከፍ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በቀጣይ አቅሙን በማጠናከር በሶስት ሽፍት እየሠራ በዓመት ከ130 ቶን በላይ የአቮካዶ ዘይት ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።
ፓርኩ በውስጥ ከፈጠረው የሥራ እድል ባለፈ በግብዓት አቅርቦት ትስስር ከሶስት ሺህ በላይ የአካባቢውን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ማድረጉን ጠቅሰው፤ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ኢንቨስተሮች የክልሉን ፀጋ ተጠቅመው እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም