አዲስ አበባ፡- ባለፉት ሶስት ወራት በጂቡቲ ወደብ በኩል ከአንድ ሚሊዮን 857ሺ 198 ቶን በላይ የተለያየ ዕቃ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ አስታወቀ፡፡
ኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ደምሰው በንቲ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የንግድ እንቅስቃሴ የሚከናወንባቸው የተለያዩ የንግድ መስመሮ ቢኖሩም አብዛኛውን የወጪና ገቢ ንግድ ዋና በር ሆኖ እያገለገለ የሚገኘው የጂቡቲ ወደብ ነው፡፡
ባለፉት ሶስት ወራትም በጂቡቲ ወደብ በኩል አንድ ሚሊዮን 857 ሺ 198 ቶን በኮንቴይነርና ከኮንቴይነር ውጪ ያለ ደረቅ ጭነት ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ ከጂቡቲ ውጪ በኬንያ ላሙ ወደብ በኩል 60ሺ107 ቶን ማዳበሪያ ተጓጓዘ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 13ሺ 246 ቶን የሚሆነው ወደ ሞያሌ ተጓጉዟል ብለዋል፡፡ ይህም ወደ ሀገር ውስጥ የገባውን አጠቃላይ ጭነት መጠን ወደ አንድ ሚሊዮን 870 ሺ 444 ቶን ከፍ እንዲል ማድረጉን አብራርተዋል፡፡
አቶ ደምሰው፤ በሩብ ዓመቱ በኢባትሎ በባሕር የተጓጓዘ ጠቅላላ ደረቅ ጭነት 669ሺ 400 ቶን ሲሆን ከዚህ ውስጥ 267ሺ 300 ቶን የሚሆነው ከኮንቴይነር ውጪ ቀሪው 402 ሺ 100 ቶን ደግሞ በኮንቴይነር የታሸገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ዳይሬክተሩ ድርጅቱ በሺፒንግ አገልግሎት ዘርፍ፣ በጭነት አስተላላፊነት አገልግሎት ዘርፍ፣ በወደብና ተርሚናል ዘርፍ የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠቱን ጠቅሰው፤ ለአብነትም በሺፒንግ አገልግሎት ዘርፍ የድርጅቱን መርከቦችንና የኪራይ መርከቦችን በመጠቀም 860ሺ 387 ቶን እቃ መጓጓዙን ገልጸዋል፡፡
ይህም አፈጻጸሙ ከ2016 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተጓጓዘው አንድ ሚሊዮን 194ሺ 451 ቶን ጭነት ጋር ሲነፃፀር በ28 በመቶ ዝቅ ያለ መሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
ተቋሙ በሩብ ዓመቱ ከሚሰጡ አገልግሎቶችና ከሌሎች የገቢ ምንጮች 20 ነጥብ 46 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ 21 ነጥን ሁለት ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን የገለጹ ሲሆን፣ 18 ነጥብ 79 ቢሊዮን ብር ለሚያከናውናቸው ሥራዎች ወጪ አድርጓል፡፡ በዚህም በሩብ ዓመቱ ሁለት ነጥብ 41 ቢሊዮን ብር ከታክስ በፊት ትርፍ ማግኘቱን አስረድተዋል፡፡
ይህም ከ2016 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ገቢ በ62 ነጥብ አራት በመቶ ፤ ወጪ በ69 በመቶ ፤ ትርፍ በ24 ነጥብ አራት በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አቶ ደምሰው አብራርተዋል፡፡
መስከረም ሰይፉ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም