አዲስ አበባ፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሩብ ዓመቱ ለ170 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መሰጠቱን የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ፡፡ በክልሉ ኢንቨስት ያደረጉ ባለሀብቶች ካፒታላቸው 43 ቢሊዮን ብር መድረሱንም አስታውቋል፡፡
የቢሮ ኃላፊ ኦንጋዬ ኦዳ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በተያዘው በጀት ዓመት ሶስት ወራት ውስጥ 200 የሚሆኑ የኢንቨስመንት ፍቃድ ጥያቄዎች ለክልሉ ቀርበው ግምገማ ተደርጎባቸው 170 ለሚሆኑት የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተሰጥቷል፡፡
ባለፈው ዓመትም ከቀረበው የኢንቨስትመንት ፈቃድ ጥያቄ 120 ለሚሆኑ ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መሰጠቱንም ተናግረዋል፡፡
እስከአሁን ድረስ በክልሉ ኢንቨስት ያደረጉ ባለሀብቶች ካፒታላቸው 43 ቢሊዮን ብር መድረሱን ገልጸው፤ በክልሉ በሶስቱ በአገልግሎት፣ በግብርና እና በኢንዱስትሪ ዘርፎች የኢንቨስትመንት ሥራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል፡፡ በክልሉ የኢንቨስትመንት ዘርፉ በቋሚ 30ሺ 400 ለሚሆኑ ዜጎች እንዲሁም በጊዜያዊነት 94ሺ 600 የለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩንም ተናግረዋል፡፡
ወደ ክልሉ ለሚመጡ ባለሀብቶች ምቹ ለማድረግ አሠራሮችን በማሻሻል የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ከዞን በቀጥታ ወደ ኢንቨስትመንት ቢሮ እንዲመጣ መደረጉን ጠቁመው፤ ቢሮው ሥራውን ዲጂታይዝ በማድረግ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ጥያቄዎች በአብዛኛው በዲጂታል መንገድ እንዲጠናቀቁ ለማድረግ እቅድ ይዞ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የአንድ ማዕከል አገልግሎትንም ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል፡፡
ኢንቨስትመንት ድጋፍ እና ክትትል እንደሚፈልግ የተናገሩት ቢሮ ኃላፊው፤ በድጋፍ እና ክትትል ሥራ ወደ ባለሀብቶቹ በመቅረብ ያሉ ችግሮችን በመለየት እገዛ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ በባለሀብቶቹ በኩል ሃላፊነትን ያለመወጣት ችግር ካለ በመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ በመስጠት እስከ መሬት መንጠቅ የሚደርሱ ቅጣቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ አመልክተዋል፡፡ አሁን ላይ ለረዥም ዓመታት መሬት ወስደው ወደ ሥራ ያልገቡ የተወሰኑ ባለሀብቶች ላይ መሬት የመቀነስ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ባለሀብቶች ወደ ክልሉ ሲመጡ የኢንቨስትመንት መሬት ተዘጋጅቶ እንደሚጠብቃቸው ጠቅሰው፤ ዞኖች ለኢንቨስትመንት የሚሆኑ 100 ሺ ሄክታር መሬት ማዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ክልሉ በተፈጥሮ ሀብት የታደለ፣ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ የሚዘንብበት እና ሰላማዊ ክልል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች ወደ ክልሉ መጥተው ቢያለሙ ራሳቸውንና ሀገራቸውን የሚጠቅሙ በመሆኑ በክልሉ እንዲያለሙ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
መዓዛ ማሞ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም