ኮርፖሬሽኑ በሩብ ዓመት ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉ ተገለፀ

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በበጀት ዓመቱ በመጀመሪያ ሶስት ወራት ውስጥ ከ300 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር ያስመዘገቡ ኢንቨስተሮች መሳቡን ገለፀ፡፡ ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮችና የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና 45 ባለሀብቶች መሳብ መቻሉ አስታውቋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽንና ማርኬቲንግ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘመን ጁነዲ እንደገለጹት፤ ባለፉት ሶስት ወራት ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የተለያዩ ሼዶችና የለማ መሬት ማስተላለፍ ተችሏል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው ኢንቨስት ካደረጉት ባለሀብቶች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት አቅም ያላቸው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ሲሆኑ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ እንደተሠማሩ ገልፀው፤ ይህም ከዕቅዱ አንፃር ከፍተኛ መሆኑን ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም የቻይና ፤ የጃፓንና የቬትናም ባለሀብቶችም ከተሳቡ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ውስጥ እንደሚገኙበት ተገልጿል። በኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው ኢንቨስት ያደረጉት ባለሀብቶች ሃዋሳ፤ ኮምቦልቻ፤ ቦሌ ለሚ እና ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ገብተው የሚሠሩ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

ለአፈፃፀሙ ከፍተኛ መሆን ባለፉት ዓመታት መንግሥት የኢንቨስትመንት ከባቢውን ምቹ ለማድረግ የወሳደቸው ማበረታቻዎች ፤ ለሀገር ውስጥ ባለ ሀብቶች የተሰጠው ትኩረት ፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ያሉ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮችና የኮርፖሬሽኑ አገልግሎት አሰጣጥ እየተሻሻለ መምጣት ዋነኛ ምክንያቶች ሆነው በሪፖርቱ ላይ ተመላክተዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት የግምገማ መድረክ የኮርፖሬሽኑ የማኔጅመንት አባላት እና የመምሪያ ኃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You