አዲስ አበባ፦ በዘንድሮ በጀት ዓመት ከ34 ሺህ ቶን በላይ ቡና ወደ ማእከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለማሪያም ተስፋዬ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ ባሳለፍነው በጀት ዓመት 24 ሺህ ቶን ቡና ከክልሉ ወደ ማዕከላዊ ገበያ የተላከ ሲሆን በ2017 ዓ.ም ይህንን ከፍ በማድረግ 34 ሺህ ቶን ቡና ወደ ማእከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየሠራን ነው።
የቡና ምርታማነት በሄክታር ሰባት ነጥብ አራት ኩንታል ከነበረበት በ2017 ዓ.ም ስምንት ነጥብ ስምንት ኩንታል በሄክታር እንደሚገኝ የቅድመ ምርት ግምት መረጃ ያሳያል ያሉት አቶ ኃይለማርያም፤ በክልሉ 229 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ቡና እንደሚለማ ገልጸዋል።
የቡና ማሣ ምርታማነት ግብ ለማሳካት ያረጁ ቡናዎችን በጉንደላና ነቅሎ በአዲስ በመተካት፣ የአረምና የኩትኳቶ ሥራ፣ ኮምፖስት ዝግጅትና አጠቃቀም ላይ የተሠሩ ሥራዎች ውጤት እያስገኙ መሆኑን ገልጸው፤ አሁን የአፈር ለምነትን የሚያሻሽሉና ለአርሶ አደሩ ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኙ ተስማሚ ደባል ሰብሎች ማልማት ላይ ትኩረት እንደተረገ ተናግረዋል።
በ2017 በጀት ዓመት ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ከታቀደው 287 የታጠበ ቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሁለት መቶ የሚሆኑት ቅድመ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል ያሉት አቶ ኃይለማርያም፤ 44 ኢንዱስትሪዎች ደግሞ ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቁመዋል።
የእሸት ቡና አሰባሰብ የተጀመረባቸው አካባቢዎችን የግብይት ሥርዓት እና የጥራት ቁጥጥር ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልጸው 25 ሺህ ቶን እሸት ቡና መለቀሙን ጠቅሰዋል፡፡
አክለውም፤ የቡና አሰባሰብ ሂደቱ ከአምና በተሻለ መልኩ በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሰበሰብና የግብይት ሥርዓት የሚከናወን መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም ተፈጻሚነት የሁሉም ማህበረሰብና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም