የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ዛሬ ይጀምራል

– በአማራ ክልል የአስተባባሪዎች ሥልጠና በቀጣይ ሳምንት ይሰጣል

ቦንጋ፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከሁለት ሺ 200 በላይ ተወካዮች የሚሳተፉበት አጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ በዛሬው እለት እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ። በአማራ ክልልም የአስተባባሪዎች ሥልጠና በቀጣይ ሳምንት እንደሚሰጥ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ እንደገለፁት፤ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥቅምት 30 በቦንጋ ከተማ በሚከናወነው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ፤ በክልሉ ከሚገኙ 57 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮችን የሚወክሉ ከሁለት ሺ 200 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ።

በክልል ደረጃ በሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ በጥልቀት በመመካከር አጀንዳዎችን የማሰባሰብና በሀገራዊ ምክክር የሚሳተፋ ተወካዮች መረጣ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

እንደ ኮሚሽነር ሙሉጌታ ገለፃ፤ በምክክር ሂደቱ ቁልፍ ከሆኑ ተግባራት መካከል አጀንዳን አካታችና አሳታፊ በሆነ ሂደት የማሰባሰብ እንዲሁም በሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጥ ተግባር ነው፡፡

በሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍም ሀገር አቀፍና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሶስቱ መንግሥት አካላት ተወካዮች፣ የተለያዩ ማህበራትና ተቋማት ተወካዮችና እንዲሁም በክልሉ የሚገኙ ምሁራንና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ዋነኛ ተሳታፊዎች እንደሚሆኑ ኮሚሽነር ሙሉጌታ ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች፣ በሲዳማ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በሐረር፣ በአፋር፣ በሱማሌ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራውን በተሳካ ሁኔታ ማከናወን መቻሉን ኮሚሽነሩ አስታውቋል

ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው በበኩላቸው እንደገለፁት፤ ኮሚሽኑ በአዋጅ በተሰጠው ሃላፊነት መሠረት በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች እየሠራ ይገኛል። በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ኮሚሽኑ ሥራዎችን የጀመረ ቢሆንም፤ ይህን ለማስቀጠል የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡

በዚህም በአማራ ክልል የአስተባባሪዎች ልየታ ተደርጎ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በተጠቃለለ ሁኔታ ከወረዳ ጀምሮ የአስባባሪዎች ስልጠና እንደሚሰጥና ከዚያም በመቀጠል የተሳታፊዎች ልየታ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

በትግራይ ክልልም ንግግሮች የተጀመሩ ሲሆን ለምክክሩ ፍቃደኝነት እንዳለ ማወቅ እንደተቻለና በቀጣይም የምክክሩ ሂደት የሚጀመር ይሆናል ሲሉ ኮሚሽነር ዘገየ አመላክቷል።

በዛሬው እለት በሚጀመረው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ተሳታፊዎች ምክክሩ የሚኖረውን ክልላዊና ሀገራዊ ፋይዳ በመረዳት በምክክሩ በንቃት እንዲሳተፉም ጥሪ ቀርቧል፡፡

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You