አዲስ አበባ፡- በ2017 ዓ.ም በሁሉም ክልሎች የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት በማልማት 172 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግኑኝነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ከበደ ላቀው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤2017 ዓ.ም በሁሉም ክልሎች የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት በማልማት 172 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡
በ2017 ዓ.ም የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት በአራት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ በማልማት 172 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በበጋ ወቅት ሁለት ነገሮችን ለማልማት ማለትም የአትክልት፣ የፍራፍሬና የስንዴ ምርቶችን በማልማት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በበልግ፣ በመኸር፤ በበጋ በሶስት ወቅቶች የግብርና ምርቶችን በማምረት ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ እየተሠራ ነው፤ በተሠራውም ሥራ ትልቅ ውጤት እየተገኘ ነው፤ በ2017 ዓ.ም የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት ለማግኘት የታቀደውን 172 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እውን ለማድረግ ለአርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ ግብዓት ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከበጋ መስኖ ልማት የሚጠበቀውን የስንዴ፤ የአትክልትና የፍራፍሬ ምርትን ለማግኘት ለአምራቹ ማህበረሰብ ሞተሮችን፣ ፓንፖችንና ለመስኖ ልማት የሚያገለግሉ ትልቅና ጉልበት ያላቸውን ሞተሮች በመግዛት በድጋፍ መልኩ ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በ2017 ዓ.ም የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት በሁሉም ክልሎች በስፋት እየተሠራ ቢሆንም በተለይ በኦሮሚያ ክልል በይበልጥ ለማልማት እየተሠራ ነው፤ በክልሉ የበጋ ስንዴ ልማት ለማልማት እየተሠራ ባለውም ሥራ እስካሁን ማለትም ከጥቅምት 19/2017 ዓ.ም ድረስ በባህላዊ መንገድ ስድስት መቶ 70 ሺህ ሄክታር መሬት፣ በኮባይነር አንድ መቶ 80 ሺህ ሄክታር በአጠቃላይ ስምንት መቶ 50 ሺህ ሄክታር መሬትን ለዘር የማዘጋጀት ሥራ ተሠርቷል፤ ለዘር ከተዘጋጀውም ከስምንት መቶ 50 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ አምስት ሺህ 113 ሄክታር መሬት የሚሆነው በዘር ተሸፍኗል ሲሉ አብራርተዋል።
አርሶ አደሩ ከበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እያገኘ ያለውን ጥቅም በመገንዘብ በግሉ ሞተሮችን፣ ፓንፖችን እየገዛ ጥቅም ላይ እያዋለ ነው፤ ምርትና ምርታማነቱንም እያሳደገ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ከበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ለማግኘት የታሰበውን ምርት ተግባራዊ ለማድረግ ልማቱን በቴክኖሎጂ የማስደገፍ፣ ምርጥ ዘር የማቅረብ፤ በልማቱ ላይ የግሪሳ ወፍና አንበጣ ተከስቶ እቅዱ እንዳይኮላሽ ለመከላከል የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው፤ ከተከሰተም ለመከላከል አምስት የርጭት አውሮፕላኖቸውና መኪናዎች ዝግጁ ናቸው ያሉት አቶ ከበደ፤ ለሰብሉ አስፈላጊውን ጥበቃና ቁጥጥር የማድረግ ሥራም የሚሠራ ይሆናል ሲሉ ጠቁመዋል።
ተግባራዊ የተደረገውን የሀገር በቀል ኢኮኖሚው ማሻሻያን ውጤታማ ለማድረግ ግብርናው ትልቅ ሚና ይጠበቅበታል፤ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የሚጠበቅበትን ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም