በብሪክስ ማሕቀፍ ውስጥ የኢትዮጵያ ተጠቃሚነት

በሩሲያ ካዛን 16ኛው የብሪክስ ጉባዔ ላይ ሰፋ ያሉ ጉዳዮች ተዳሰውበታል፡፡ ኢትዮጵያም ተጠቃሚነቷን ለማስፋት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተመራ ልኡካን ተወክላም ነበር፡፡ ባለፈው ዓመት በተካሄደው ጉባዔ ኢትዮጵያን ጨምሮ ስድስት ሀገራት ብሪክስን መቀላቀላቸው ይታወሳል፡፡ ብሪክስ ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 የሚደርሱ የሀገራት ስብስብ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የዓለማችን 45 በመቶ የሕዝብ ብዛት እና 35 በመቶ የዓለምን ኢኮኖሚ የያዙ ሀገራትን አሰባስቧል፡፡ ብሪክስ በተለያዩ የትኩረት መስኮች ላይ ትብብር የሚያደርግና የጋራ አቋም የሚያዝበት በመሆኑ ኢትዮጵያ የዚህ አባል መሆኗ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ አይነተኛ መንገድ ከፍቶላታል፡፡

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ አዘጋጅነት ‹‹በብሪክስ ማሕቀፍ ውስጥ የኢትዮጵያ ሚና›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ እንደተገለጸው፤ ብሪክስ የፖለቲካና የጸጥታ፣ የኢኮኖሚና የፋይናንና የሕዝብ ለሕዝብና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር በመሆኑ እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላሉ ሀገር ብዙ ጠቀሜታ አለው። የትብብሩ መገለጫዎች ከሆኑት መካከል አዲስ የልማት ባንክ ተቋቁሟል።

ባንኩ ለታዳጊ ሀገራት ለመሠረተ ልማትና ለዘላቂ ልማት የገንዝብ ድጋፍና የፋይናንስ አቅርቦት የሚያደርግ ነው። ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. ከ2015 ጀምሮ እስከ 2021 25 ቢሊዮን ዶላር ለሀገራቱ አቅርቧል። ባለፈው ዓመት ብቻ አምስት ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ያቀረበ ሲሆን የስብስቡ ውጤታማነት አንድ ማሳያ ነው። በቀጣይ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የእድገት ጉዞ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞትዮስ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ብሪክስን የተቀላቀለችው ብሔራዊ ጥቅሟን ይበልጥ ለማሳደግ ነው። የብሪክስ ስብስብ እየተጠናከረ ሲሄድ ብዙ ሀገራት ብሪክስን የመቀላቀል ፍላጎት አሳይተዋል። ተደጋጋሚ ጥያቄዎች እያቀረቡም መጥተዋል። በነባር የስብስቡ ሀገራት መካከል የትኞችን ሀገራት ማካተት አለብን? እና አዲስ አባል ሀገራትን በምን መንገድ መቀበል እንደሚገባ ሰፊ ውይይት አድርገዋል። በመጨረሻም የስብስቡን ዓላማ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ተፅዕኖ ፈጣሪ ናቸው ያሏቸውን ሀገራት ብቻ ተቀብለዋል። ከዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ናት፤ ይህም የሚያሳየው በዓለም ደረጃ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት ከፍተኛ መሆኑን ነው።

ኢትዮጵያ ብሪክሰን የተቀላቀለችበት ሦስት ምክንቶች አሏት ያሉት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በፍጥነት በማደግ ላይ ኢኮኖሚ ባለቤት ናት። እድገትን ለማሳለጥ የቴክኖሎጂ፣ የፋይናንስ ድጋፍና ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል። ከላይ የተጠቀሱትን ለማግኘት የብሪክስን ስብስብ መቀላቀልና ስብስቡ ይዞት የሚመጣውን እድል ለመጠቀም መፈለግ ከምክንያቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን ያመለክታሉ።

ሁለተኛው ምክንያት ወሳኝ በሆኑ ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ላይ የሚመካከርና የጋራ አቋም የሚይዝ ስብስብ ሲሆን በተለይ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ ምን መምሰል አለበት በሚለው፣ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ይበልጥ አካታች፣ ፍትሐዊ እንዲሆኑ፣ የታዳጊ ሀገራትን ፍላጎት የሚያሟሉና ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ እንዴት መሻሻል በሚኖርባቸው ጉዳዮች ላይ አቋም የሚያዝበት ስብስብ በመሆኑ ነው። ኢትዮጵያ የዚህ ስብስብ አባል በመሆን ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበርና የአፍሪካን ፍላጎትና ድምጽ ለማሰማት የምትችልበት ጠቃሚ እድል ይፈጥራል ብለዋል።፡

እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመን ያስቆጠረ የዲፕሎማሲ ታሪክ ያላት ሀገር ናት። በርካታ የዓለም ሀገራት ችግር ውስጥ በነበሩበት ጊዜ የሊጎፍኔሽን አባል ነበረች። ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ነጻ ባልነበሩበት ጊዜ በርካታ የዲፕሎማሲ ታሪክ ያላት በመሆኑ በብሪክስ ስብስብ ውስጥም ለአፍሪካ ሀገራት ድምጽ ለመሆን ወደ ስብስቡ ገብታለች። እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራች አባል ሀገር ናት። ይህን ታሪክና ባህል በማስቀጠል ዓለም አቀፍ ሥርዓቱ ማስተካከልና የአፍሪካን ድምጽ በመሆን ለመሳተፍ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የብሪክስ ስብስብ ውስጥ ኢትዮጵያ አባል ባትሆን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በተቃራኒ መንቀሳቀስ ለሚፈልጉ አካላት ሜዳው ይለቀቃል። ኢትዮጵያ በሌለችበት በኢትዮጵያ ላይ የፈለጉትን አቋም ሊያራምዱ ይችላሉ። ይህን አይነት አሉታዊ እንቅስቃሴ ለመከላከል በብሪክስ ማሕቀፍ ውስጥ መገኘት ለብሔራዊ ጥቅም በጣም ወሳኝ ነው። አባል ለመሆን የተደረገው ጥረትም ተሳክቶ ውጤት እያመጣ መሆኑንም ሚኒስትሩ ይጠቅሳሉ።

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ለመሆን ከደቡብ አፍሪካው ስብስባ ቀደም ብሎ በርካታ የዲፕሎማሲ ሥራ ሠርታለች። ኢትዮጵያ የሌለችበት ስብስብ አፍሪካን ሰብስቤያለው ብሎ መውሰድ እንደማይቻል የማስረዳት ሥራ በሚገባ የተሠራ ሲሆን ውጤት አምጥቷል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአፍሪካ ህብረት ምሥረታ፣ ለአፍሪካና ለዓለም ሰላም የነበራት ሚና፣ የሕዝብ ቁጥር ብዛት፣ እያስመዘገበች ያለው የኢኮኖሚ እድገት፣ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗ ግምት ውስጥ በመግባት አባል እንድትሆን የተደረገው ጥረት ለውጤታማነቱ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ።

እንደ አምባሳደር ሬድዋን አባባል፤ የብሪክስ አባልነት ብዙ ጥረትን የጠየቀና ሊቀር የሚችልበት እድልም ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ደቡብ ለብሪክስ አባል ሀገራት መሪዎች ኢትዮጵያ በአፍሪካና በዓለም ደረጃ ያላትን ተጽዕኖ በመግለጽ ያደረጉት ጥረት ጉልህ ነው። አሁን ላይ አዲስ ለአባልነት የሚጠይቁ ሀገራትን የማስገባትና ያለማስገባት ሁሉም ድምጽ በድምጽ የመሻር መብት አለው። ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት የስብስቡ አባል ባትሆን ከነጭራሹ የማትገባበት እድል ነበር። ብሪክስ ከኢኮኖሚ ደረጃ አንጻር፣ በፖለቲካ አማራጭነት፣ በደቡብ ለደቡብ ትስስር፣ የገንዝብ ርዳታ ከማግኘት አንጻር ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ነው። አባል መሆን በዓለም መድረክ ተጽእኖን ይጨምራል፣ ወዳጅ የማብዛት አቅም፣ ኢንቨስትመንትንና የገንዝብ ድጋፍን ያሳድጋል።

ሞገስ ጸጋዬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You