ወጣቶች በመዲናዋ የተሠሩ የቱሪስት መስሕቦችን እንዲጎበኙ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፡- ወጣቶች በመዲናዋ የተሠሩ የቱሪስት መስሕብ መዳረሻዎችን በመጎብኘት ሀገራቸውን የማወቅ ጥረታቸውን እንዲያሳድጉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባሕል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ጥሪ አቀረበ።

የቱሪዝም ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ45ኛ በኢትዮጵያ ለ37ኛ ጊዜ ‹‹ቱሪዝም ለሠላም›› በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ይገኛል፡፡

የቢሮው ኃላፊ ሒሩት ካሣው (ዶ/ር) ትናንትና በዓሉ ሲከበር እንደተናገሩት፤ ወጣቶች በመዲናዋ የተሠሩ የቱሪስት መስሕብ ቦታዎችን በመጎብኘት ሀገራቸው ያላትን ባሕል፤ ቅርስና የተፈጥሮ የቱሪስት መስሕብ ቦታዎችን ማወቅ ይገባቸዋል።

ወጣቶች ስለሀገራቸው ያወቁትን ለሚያውቁት በማስረዳት የሀገራቸው የቱሪዝምና የሠላም አምባሳደር ሊሆኑ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ወጣቶች ሀገራቸው ያላትን እምቅ ባሕል፤ ቅርስ፣ ታሪክና የተፈጥሮ የቱሪስት መስሕብ ቦታዎችን ጎብኝተው ካላወቁ፤ ከሌላ ሀገር ለሚመጠው ጎብኚዎች ማስረዳት አይችሉም፤ ስለዚህ ሀገራቸው ያላትን የቱሪዝም ሀብት ለዓለም ለማሳወቅ የጉብኝት ባሕላቸውን ማዳበር አለባቸው ብለዋል፡፡

የሀገርን ታሪክ፣ ባሕል፣ ቅርስና የተፈጥሮ የቱሪስት መስሕብ ቦታዎችን ጎብኝቶ ማወቅ ሀገርንና ሕዝብን ማወቅ ነው ያሉት ሒሩት (ዶ/ር)፤ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች በመዲናዋ የተሠሩ የቱሪስት መስሕብ መዳረሻዎችን በመጎብኘት የቱሪዝም ዘርፉን ሊያግዙ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

ወጣቶች ከተማዋን ጎብኝተው ካላወቁ ሌላውን ጉብኝት ማስረዳት ብቻ ሳይሆን በፍቅርና በሠላም ለመኖረው ይቸገራሉ ያሉት ኃላፊዋ፤ አንዱ የአንዱን ባሕል አውቆ በሠላም፣ በፍቅርና በአንድነት ለመኖር የጉብኝት ባሕልን ማሳደግ አስፈላጊ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ወጣቱ ሀገሩ የበርካታ ባሕል፣ ቅርስና ታሪክ ባለፀጋ መሆኗን ባወቀ ቁጥር የተፈጠረበትና እየኖረበት ያለው ማኅበረሰቡ ጥበብ ያለው፣ ደግ፤ ተባባሪና መልካም ሕዝብ መሆኑን እንዲረዳ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

የሀገሩን ታሪክንና ባሕሉን የሚያውቅ ወጣት የበለፀገች ሀገር ለመፍጠር ያለውን ራዕይ እውን ለማድረግ ይችላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባ በርካታ መስሕቦች የተገነቡባት፤ የፅዳትና የውበት ተምሳሌት ናት፤ የመስሕብ መዳረሻ፤ ፅዳትና ውበት ተምሳሌነቷም ለኗሪውና ለቱሪስቶች የሚመጥን፣ ምቾትን ያረጋገጠ ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ መዲናዋን ከመውጫና ከመግቢያነት ወደ ቱሪስት ከተማነት ቀይሯታል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ቱሪዝም ባሕልን፤ ተፈጥሮን፣ ኪነ-ጥበብን፣ ቅርስን በአጠቃላይ ታሪክን መሠረት አድርጎ የሚጎበኝ የአንድ ማኅበረሰብ ማንነት የሚገለጥበት መድረክ ነው ያሉት ሒሩት (ዶ/ር)፤ በመዲናዋ የሚገኙ ባሕሎች፣ ቅርሶችንና ታሪክን ለዓለም ከማስተዋወቅ ባለፈ ለኢኮኖሚ ምንጭነት እንዲውሉ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።

መልካም እንግዳ ተቀባይነት የቱሪስት ፍሰትን ያሳድጋል፤ መልካም እንግዳ ተቀባይነታችን የቱሪስት መስሕብነትን የሚያሳድግ ባሕላችን ነው፤ የእንግዳ ተቀባይነት ባሕላችንን አጠናክረን ማስቀጠል አለብን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You