አዲስ አበባ፦ በሚቀጥሉት 10 ቀናት በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ እንደሚስተዋል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በሌላ በኩል በደቡብ ምዕራብ፣ በደቡብና በደቡብ ምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የዝናቡ መጠንና ስርጭት ቀጣይነት እንደሚኖረው ገልጿል።
ኢንስቲትዩቱ ለኢፕድ በላከው መግለጫ፤ በሚቀጥሉት ቀናት ዝናብ ሰጭ የአየር ሁኔታ ክስተቶች በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ እንዲሁም በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የተሻለ ገጽታ እንደሚኖራቸው አመላክቷል።
በመሆኑም በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የቦረናና ጉጂ ዞኖች፤ የሲዳማ ክልል ዞኖች፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች እና የሶማሌ ክልል ደቡባዊ ዞኖች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው አኃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ ሲል ኢንስቲትዩቱ ገልጿል፡፡
በተጨማሪም አልፎ አልፎ ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት በአማራ ክልል፤ በኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን፤ በትግራይ ክልል፤ በአፋር ክልል፤ በኦሮሚያ ክልል፤ በአዲስ አበባ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች ወቅቱን ያልጠበቀ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ብሏል፡፡ ስለሆነም በሚኖሩት ደረቅ ቀናቶች የደረሱ ሰብሎች መሰብሰብ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁሟል።
በሌላ በኩል በሚቀጥሉት 10 ቀናት የሚኖረው እርጥበት ቀደም ብለው ለተዘሩና ፍሬ በማፍራት ላይ ለሚገኙ ሰብሎች፣ ዘግይተው ተዘርተው በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሰብሎች፣ ለቋሚ ተክሎች እንዲሁም በመኸር ወቅት መጨረሻ ላይ በአፈር ውስጥ በተከማቸ እርጥበት በመታገዝ ለሚዘሩ እንደ ጓያ እና ሽንብራ ለመሳሰሉ የጥራጥሬ ሰብሎች የተሟላ እድገት እንዲኖራቸው ከማድረግ አንፃር አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው መግለጫው ገልጿል።
በውሃው ዘርፍ ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተፅዕኖ የተገለጸ ሲሆን፤ በዚህም በአብዛኛው ገናሌ ዳዋ፣ ዋቤ ሸበሌ፣ ኦሞ ጊቤ፣ ባሮ አኮቦ፣ የታችኛው ዓባይ፣ የመካከለኛው እና የታችኛው ስምጥ ሸለቆ ተፋሰሶች ላይ ከእርጥበታማ እስከ ከፍተኛ የእርጥበት ሁኔታ እንደሚያገኙ ተጠቅሷል።
በተጨማሪም በመካከለኛው እና በታችኛው ተከዜ እንዲሁም አዋሽ ተፋሰሶች ላይ መጠነኛ እርጥበት እንደሚያገኙ ጠቁሟል።
የሚኖረው የእርጥበት ሁኔታም የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር የውሃ ሃብትን ግብዓት በማሻሻል ለዘላቂ የውሃ ሀብት ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ በሌላ በኩል በአብዛኛው አፋር ደናክል፣ የላይኛው ተከዜ እንዲሁም የታችኛው አዋሽ ምሥራቃዊ ክፍል ደረቅ የአየር ሁኔታ ስር ሆነው እንደሚቆዩ ተገልጿል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23 ቀን 2017 ዓ.ም