ጉባዔው ከ9 ሺህ በላይ አቤቱታዎች ቀርበውለት 6 ሺ 283ቱን መርምሯል

– 138ቱ የሕገ መንግሥት መብት ጥሰት የተፈጸመባቸው ናቸው

አዲስ አበባ፡- የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን ማጣራት ከጀመረበት ከ2006 ዓ.ም ጊዜ አንስቶ ከዘጠኝ ሺህ በላይ አቤቱታዎች ቀርበውለት እስከ ጥቅምት አጋማሽ ስድስት ሺህ 283ቱን መመርመሩን አስታወቀ፡፡ ከመረመራቸው መዝገቦች ውስጥ 138ቱ የሕገ መንግሥት መብት ጥሰት የተፈጸመባቸው መሆናቸው መረጋገጡን ገልጿል።

የጽሕፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ ወዬሳ በተለይ ለኢፕድ እንደተናገሩት፤ ጽሕፈት ቤቱ ከመረመራቸው ስድስት ሺህ 283 መዝገቦች ውስጥ 138ቱ የሕገ መንግሥት መብት ጥሰት የተፈጸመባቸው በመሆናቸው ለመጨረሻ ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርቧቸዋል።

በ2016 በጀት ዓመት ከቀረቡለት አንድ ሺህ 835 አቤቱታዎች መካከል አንድ ሺህ 686ቱ ላይ አስፈላጊ ውይይት በማድረግ የሕገ መንግሥት ጥሰት የተፈጸመባቸው 24 አቤቱታዎችን ለይቶ ለመጨረሻ ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መላኩንም አስታውሰዋል፡፡

በ2017 በጀት በሩብ ዓመቱ ጉባዔው 309 አቤቱታዎች መርምሮ ከእነዚህ ውስጥ ስድስቱ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በማለት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀረበ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራርና የመንግሥት አካላት ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ ጋር መጻረር እንደሌለባቸው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ዘጠኝ የተደነገገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጽሕፈት ቤቱ የተሰጠውን ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን የማጣራት ተልዕኮ እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የትኛውም ተቋምም ሆነ ግለሰብ የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት እንዳለበትም አስረድተዋል።

የአቤቱታ መዝገቦች ሲቀርቡ ካሉት የሕገ መንግሥት ተመራማሪዎችና ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሕግ ምሑራን ጋር ጥልቀት ያለው ውይይትና ምርመራ እንደሚያካሂድም ገልጸዋል፡፡

ዳይሬክተሩ እንዳስታወቁት፣ በሕገ መንግሥት ትርጉም ሥራ ላይ ከምርምር ሥራ ላይ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ተባብሮ ለመሥራት እንዲሁም ጉባዔው የሚሠራቸውን ሥራዎች ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል የአሠራር ደንብ ሥርዓት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርቦ በ2016 መፅደቁን አንስተዋል።

ጽሕፈት ቤቱ ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም የመስጠት ተልዕኮውን መወጣት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያለፈው 2016 በጀት ዓመት አፈጻጸሙ በታሪኩ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበበት መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ፣ አፈጻጸሙን ከ300 ከመቶ በላይ ያሻሻለበትን የዜጎች ንብረት የማፍራት፣ በሕግ ፊት እኩል የመዳኘትና ሌሎችም ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸውን በማረጋገጥ ረገድ ውጤት መገኘቱንም ጠቁመዋል።

ጽሕፈት ቤቱ ያለፈው ዓመት ጠንካራና ደካማ ጎኑን ግምገማ መነሻ በማድረግ፣ በያዝነው በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ እቅድ ይዞ እየሠራ መሆኑን አመላክተዋል።

የተወዘፉ መዝገቦችን በአጭር ጊዜ ውስጥ መርምሮ ምላሽ መስጠት የሚያስችል አሠራርም አስቀምጦ ወደ ተግባር የገባ ሲሆን፣ አቤቱታ አቅራቢው በአካል መገኘት ሳይጠበቅበት ካለበት ሆኖ አቤቱታውን እንዲያቀርብ የሚያስችል አሠራር እየዘረጋ ይገኛል ብለዋል፡፡

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You