ከግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ 976 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል

አዲስ አበባ፡ ባለፉት ሦስት ወራት ከግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ 976 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡ ለማዳበሪያ ግዥ የሚውል 156 ቢሊዮን ብር መፈቀዱ ተመላክቷል።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በ2017 በጀት ዓመት በ100 ቀናት እቅድ አፈጻጸም የተገኙ ዋና ዋና ስኬቶች ላይ ትናንት መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በሦስት ወራት ከግብርና የወጪ ንግድ ምርቶች አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዶ 976 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡

ገቢው ከፍተኛ መሆኑ ትልቅ ስኬት መሆኑን ሚኒስትሩ አስታውቀው። ሰሊጥ፣ ለውዝ፣ አኩሪ አተር እና ሌሎችም ቀድሞ ከነበራቸው የምርት ሁኔታ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየታቸውን አስረድተዋል።

በግብርናው ዘርፍ በዚህ ዓመት ስድስት ነጥብ አንድ በመቶ ዕድገት ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተው፤ ለዚህም አስፈላጊው ሥራ ሁሉ እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።

ባለፈው ዓመት ከቡና ምርት ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን አስታውሰው፤ በተያዘው ዓመትም ከቡና ምርት 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡

በመኸር እርሻ በዘር ከተሸፈነው 20 ሚሊዮን 235 ሺህ 184 ሄክታር መሬት ውስጥ አንድ ሚሊዮን 793 ሺህ 931 ሄክታር መሬት ላይ ያለ የደረሰ ሰብል ተሰብስቦ አምስት ሚሊዮን 305 ሺህ 380 ኩንታል ምርት ተገኝቷል ብለዋል፡፡

በ2017 የምርት ዘመን መስኖ ስንዴ በሁሉም ክልሎች አራት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማረስ እና 173 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱንም ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት በክረምት እና በበጋ ስምንት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ ምርት በመሸፈን 3 መቶ ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ለማግኘት ታቅዷል፡፡

በዚህ ሩብ ዓመት 512 ሺ 216 ነጥብ ዘጠኝ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ለተጠቃሚዎች ማሰራጨት መቻሉን ተናግረው፤ ለ2017/18 የምርት ዘመን ለመስኖ፣ ለበልግ እና ለመኸር የሚውሉ “ዩሪያ” እና “ዳፕ” በአጠቃላይ ሁለት ሚሊዮን 404 ሺ 729 ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

ለ2017/18 የምርት ዘመን ለማዳበሪያ ግዥ 156 ቢሊዮን ብር መፈቀዱን አስታውቀው፤ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ምርጥ ዘር ለማቅረብ በዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት በሌማት ትሩፋት ምርቶች የአምስት ነጥብ አራት በመቶ ዕድገት ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በተያዘው ዓመት 12 ቢሊዮን ሊትር የወተት ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሮች ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል እቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You