የአፄ ቴዎድሮስ ጋሻ ከ156 ዓመታት በኋላ ወደኢትዮጵያ ተመለሰ

አዲስ አበባ፡- በመቅደላ ጦርነት ወቅት ተዘርፎ ወደ እንግሊዝ ሀገር የሄደው የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ጋሻ ከ156 ዓመታት በኋላ ትናንት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል፡፡ የተዘረፉ ቅርሶችን ለማስመለስ የሚደረገው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል፡፡

ቅርሱ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ ርክክብ ተደርጎ ወደ ብሔራዊ ሙዚየም የገባ ሲሆን ቅርሱን ለማስመለስ ከአንድ ዓመት በላይ የሚፈጅ ጥረት መደረጉን በርክክቡ ወቅት ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው በዕለቱ እንደገለጹት፤ ቅርሶች የሀገርና የትውልድ ምልክት በመሆናቸው የተዘረፉትን ለማስመለስ ጥረት ማድረግ ይገባል፡፡

ቅርሱ ከአንድ ዓመት በፊት በእንግሊዝ ለጨረታ ቀርቦ የነበረ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ጨረታ ያወጣው ተቋም ጨረታውን ለመሰረዝ ፈቃደኛ ያልነበረ ቢሆንም ጋሻው የአንድነት፣ የነፃነትና የክብር ተምሳሌት በመሆኑ በተወሰደ ጠንካራ አቋም ሊስማማ ተገዷል ብለዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የተዘረፉ ቅርሶች መመለሳቸው ለቱሪዝሙ ዘርፉ ያለው አስተዋፅዖ ከፍተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ቅርሱ በልዑል ኤርሚያስ ሣሕለ ሥላሴ ኃይለ ሥላሴ እና በኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለአደራ ድርጅት ግዢ ተደርጎ ወደ ኢትዮጵያ ሊመለስ ችሏል፡፡

ቅርሱ በኦንላይን ጨረታ እንደወጣ ጥቆማ ከደረሰ

በኋላ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ጨረታው እንዲቆም በጻፈው ደብዳቤ መሠረት ከኢትዮጵያ ቅርስ አስመላሽ ብሔራዊ ኮሚቴ እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ጥረት መደረጉንም አብራርተዋል፡፡

ቅርሱ ከ156 ዓመታት በፊት ከመቅደላ ተዘርፎ የተወሰደ ነው ያሉ ሲሆን፤ በቀጣይም በየትኛውም አጋጣሚ ከሀገር የወጡ ቅርሶች ለማስመለስ ትኩረት መደረጉን አስረድተዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ቅርሶች የት የት እንደሚገኙ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሕግ አግባብ የሚመለሰውን በሕግ በዲፕሎማሲ ጥረት የሚመጣውን በዲፕሎማሲ ለማስመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።

ቅርሱ ከኢትዮጵያ ስለመሆኑ መቅደላን ጠቅሶ የተዘረፈበት ጊዜ የሚያሳይ ምልክት እንዳለውም ነው አንስተዋል፡፡

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በበኩላቸው፤ ብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት ቅርሶችንና የቀደሙ ታሪኮች በአግባቡ በመረዳት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት የተዘረፉ ቅርሶች ለማስመለስ የሚደረገው ጥረት ይበል የሚያሰኝ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ቅርሶች የሉዓላዊነትና የአልደፈር ባይ ኢትዮጵያውያን የማንነት መገለጫ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ጋሻውን ለማስመለስ የብዙ ሰዎችና ተቋማት ጥረት ታክሎበት ወደ ኢትዮጵያ በግዢ እንዲመጣ ተደርጓል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባል አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ጨረታ ያወጣው ተቋም ጨረታውን እንዲሰርዝ የተለያዩ ዓለም አቀፍና ታዋቂ ሚዲያዎች፣ የፓርላማ አባላት እንዲሁም ታዋቂ ሰዎች ጫና እንዲደርጉ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You