ዜና ሐተታ
አቶ ሚልኪያስ ሳጣ የወላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ተወካይ ናቸው። በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘውን የባለድርሻ አካላት ምክክር መድረክ ፓርቲያቸውን ወክለው ሲሳተፉ ነው ያገኘናቸው።
እንደ ፓርቲ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር፣ አንድነትን ለማፅናት፣ የሀገር ሠላምን ለማረጋገጥ፣ ግጭት ለማስወገድና ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ሀገራዊ ምክክሩ ወሳኝና ወቅታዊ ነው የሚል አቋም አለን ይላሉ።
በዚህ መነሻነትም በፓርቲ ደረጃ እየተሳተፍን ነው። እንደ ፓርቲ ለሕዝባችን የምናስብና ለሀገራችን የምንቆረቆር ከሆነ በአሁኑ ጊዜ የሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ትልቁ አጀንዳችን ሊሆን ይገባል የሚሉት አቶ ሚልኪያስ፤ በሀገራዊ ምክክሩን ዳር ሆነው የሚመለከቱ አንዳንድ ፓርቲዎችና ግለሰቦች መኖራቸውን ይጠቁማሉ። ይህ ትክክል አይደለም። ምክንያቱም መሠረታዊ ሀገራዊ ችግሮች እንፍታ ካልን ሃገራዊ ምክክሩ አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው ያለው ሲሉ ይናገራሉ።
ሀገራዊ ምክክር አካሂደው የሀገራቸውን መሠረታዊ ችግሮች ከፈቱ ሀገራት ጎራ ለመሰለፍ እንደ ጅማሮው በቀጣይም አሳታፊነትና አካታችነቱን ጠብቆ በቅንነት የሚካሄድ አለበት። ይህን ማድረግ ከቻልን ሀገራዊ ምክክርን ያሳኩ ሌሎች ሀገራት ስላሉ እኛም የማናሳካበት ሁኔታ የለም ሲሉ ይገልፃሉ።
እንደፓርቲ በምክክሩ ወደ ተሻለ ሀገራዊ መግባባት አንመጣለን ብለን ተስፋ አድርገን ነው የሚለውን ሀሳብ ይዘን ነው እየተሳተፍን የምንገኘው ከሀገራዊ ምክክሩ መሸሽ የሚያስኬድ አይደለም። ሁላችንም የሀገራችን ችግሮች የሚያሳስቡንና ለሕዝባችን ዘላቂ ሠላም የምንሻ ከሆነ ባይተዋር የምንሆንበት ጉዳይ አይደለም። በመቀራረብ በመነጋገር ለሀገራዊ አንድነት፣ መግባባትና ሠላም አበክረን መሥራት፣ መሳተፍና ማገዝ ይኖርብናል ይላሉ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለረጅም ዘመናት ተስማምቶ፣ ተጋምዶና ተዋልዶ የኖረ ሕዝብ ነው የሚሉት አቶ ሚልኪያስ፤ በመነጣጠል፣ በመከፋፈል፥ በመበላላት የምናመጣው አንዳችም ትርፍ አይኖርም ሲሉ ይገልጻሉ። ስለዚህ እንደ ሕዝብ አንድነት መፍጠር መቀራረብ ከዚህ በፊት የነበሩትን የሚያቀራርቡ መልካም እሴቶችን ሁሉ ማጠናከር ለሀገር ግንባታና አንድነት ለማዋል ምክክር አይነተኛ መፍትሔ እንደሆነ ያስረዳሉ።
በጥላቻ በጦርነት እንደ ሀገር፥ እንደ ሕዝብና እንደ ግለሰብ ከወድመት ውጭ የምናመጣው ለውጥ አይኖርም። እንደበፊቱ ተስማምተን ተጋግዘን ተባብረን ይችን በተፈጥሮ ሀብት የተቸረችን ሀገር ማልማት የሕዝቡን ሕይወት መቀየር ይኖርብናል ሲሉም ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።
የቁጫ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በመወከል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በክልል ደረጃ የባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ሊሳተፍ እንደመጡ የገለጹልን ደግሞ አቶ በቀለ አበራ ናቸው። በአሁኑ ጊዜም ኢትዮጵያን ካለችበት የችግር አረንቋ እንዴት እናውጣት እና ሕዝቦቿ እንዴት ማሻገር ይቻላል የሚል ትልቅ ሀገራዊ ምክክር እየተካሄደ መሆኑን ይናገራሉ።
አሳታፊና አካታች ሆኖ ከታች ጀምሮ የችግሩን ምንጭ አውቆ መፍትሔ ለመስጠት የሚካሄደው ምክክር ይበል የሚሰኝ የሚደገፍ ነው የሚሉት አቶ በቀለ፤ እኛም እንደ ፓርቲ ተቀባይነት ያለውና ሁሉም የሚደግፈው ተግባር ነው የሚል አቋም አለን ይላሉ። ወደፊትም በዚሁ ግልጸኝነት ከተካሄደና ተነቅሰው የወጡ መሠረታዊ ሀገራዊ ችግሮች በምክክሩ መፍትሔ የሚሰጣቸው ከሆነ ስኬታማ ምከክር ይሆናል የሚል እምነት አለን ነው ያሉት።
ሀገራዊ ምክክር ለሀገራችን ችግሮች ሁነኛው መፍቻ መንገድ ነው የሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተፈራ ታርጮ ናቸው። ሀገራዊ ምክክሩ ለአሁኑ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድ የሚበጅ ይሆናል ብለን እየሠራን ነው። የተሳካ እንዲሆንም የበኩላችንን ድርሻ እየተወጣን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የሀገር ችግርን ለመፍታትና ዲሞክራሲ ስር እንዲሰድ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊ ምክክሩ በመሳተፍ የበኩላቸውን ታሪካዊ አሻራ ማኖር ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት። ምክንያቱም ፓርቲዎች ራሳቸውን ለሀገራዊ ውስብስብ ችግሮችን እንዲፈቱ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ የመፍትሔው አካል ለመሆን መዘጋጀት አለባቸው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል። በምክክር የተገኙ መፍትሔዎችን በመተግበር ረገድም የመንግሥት ቁርጠኝነት ሊኖር ይገባል።
በአሁኑ ጊዜም በደቡብ ኢትዮጵያ በክልል ደረጃ የፖለቲካ ፖርቲዎች የመንግሥት አካላትና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የወከሉ ተመራጮችና የባለድርሻ አካላት የውይይት ምክክር ተካሂዷል።
እስካሁን በክልል ደረጃ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ በተካሄደባቸው ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች 932 ወረዳዎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች በምክክሩ መሳተፋቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።
በደቡብ ኢትዮጵያ በክልል ደረጃ የአጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ከጥቅምት 18 ቀን ጀምሮ መካሄዱ ይታወሳል መካሄዱ ይታወሳል። በአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፉ የፖለቲካ ፖርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቨል ማኅበረሰብ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎችና ሌሎች የተመረጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ተሳትፈዋል።
ጌትነት ምሕረቴ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23 ቀን 2017 ዓ.ም