አንዳንድ ቀን አለ። የቀን ጎዶሎ ይሉት ክፉ። ካላሉት ጥግ የሚያውል፣ ካላሰቡት መከራ የሚጥል። ካልገመቱት፣ የሚሰድ፣ ካላቀዱት ስር የሚወሽቅ። ይህን ቀን ደጋግመው ‹‹አይጣል! አያድርስ›› ቢሉት ከመሆን ይዘል አይመስልም። ደርሶ የነበረን ፀጋ ሲገፍ፣ ክቡር ሕይወትን ሲነጥቅ፣ ታሪክን ቀይሮ ‹‹ነበር›› ብሎ ሲያስነግር ፈጽሞ አይዘገይም። ሁሌም ድንገቴው ክስተት ካላሰቡት ችግር ይጥላል፣ ካልገመቱት መከራ ያገናኛል።
ይህ አይነቱ ቀን ብርሃንን አጨልሞ ከጽልመት ሲያዋድድ፣ የእጅ ሲሳይን ነጥቆ ዕምነት ተስፋን ሲያስቆርጥ በእጅጉ ፈጣን ነው። በሰከንድ አፍታ፣ በአንድ ጀምበር እይታ የዓመታት ልፋትን እንዳልነበር ያደርጋል። የላብ የጉልበትን ዋጋን ያስጥላል ።
ወዳጆቼ! የጉዳዩን ግዝፈት ለመግለጽ ያህል ጥቂቱን እውነት እንዲህ ጠቆምኩ እንጂ ስለ ድንገተኛ አደጋ ክፋት ከዚህም በላይ ማለት በተቻለ ነበር። አዎ! ድንገተኛ አደጋ ከቃል፣ ከንግግር በላይ ነው። የክስተቱ ቅጽበታዊነት ሁሌም ቢሆን ከአዕምሮ በላይ ይሆናል።
ድንገተኛ አደጋ በተፈጥሮም ይሁን በሰው ሠራሽ ችግሮች ሊፈጠር ይችላል። ክስተቱ ሁሌም ከጉዳት ጋር ነውና ለተጎጂውም ይሁን አይቶ ለሚሰማው ሁሉ ከማስደንገጥ በላይ ልብ ሰባሪ ነው። እንዲህ አይነቱ ድንገቴ ችግር ባጋጠመ ጊዜ ማንም ቢሆን ሕይወትን ብሎም ንብረትን ለመታደግ የአቅሙን ያደርጋል። የመኪና አደጋ ከሆነ፣ በስፍራው የደረሱ ሌሎች፣ የተጎጂዎችን ሕይወት ለማትረፍ ይፈጥናሉ። የእሳት አደጋም ቢሆን እንዲሁ። በቅርቡ በተፈጥሮ የመሬት መንሸራተት ጎፋ ላይ በደረሰው ድንገተኛ አደጋ በርካታ ወገኖቻችን ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ሕጻናትን ያለአሳደጊ፣ አረጋውያንን ያለጧሪ አስቀርቶ ቤት ያዘጋው ይህ አደጋ ታዲያ የብዙ ሰዎች መልካምነት የታየበት ነበር። አንዳንዴ ደግሞ ከእንዲህ መሰሎቹ ክፉ ቀናት ጋር ድርጊታቸውን ለማሰብ የሚከብዱ ክፉ ሰዎች ጭምር በእኩል ይወለዳሉ።
እነዚህ በግብራቸው ‹‹ክፉና ጨካኝ›› ይሉት ስያሜ የሚያንሳቸው ግለሰቦች በድንገቴ አደጋዎች ግዜ ማንነታቸው በገሐድ ይገለጻል። ሁሌም ወደስፍራው ፈጥነው ሲደርሱ እንደሌሎቹ ከአደጋው ሕይወትና ንብረትን ለመታደግ አይደለም። የእነሱ ንስር ዓይኖች ከብዙኃኑ እይታ ይለያሉ። እግር እጆቻቸው የሚዘወሩት ለእርዳታ፣ አልያም ለበጎ ተግባር አይደለም።
‹‹ግርግር ለሌባ ያመቻል›› እንዲሉ ዓላማና ግባቸው ዝርፊያና ዝርፊያ ብቻ ነው። ፈጽሞ ያዩትን አያልፉም። ካመቻቸው ቦታ፣ ከደረሱበት ስፍራ ዘው እያሉ ያገኙትን ይዘርፋሉ። ጭካኔያቸው ደግሞ በአደጋው ሕይወታቸው ካለፈ ሰዎች ኪስን እስከ መበርበር፣ ወርቅ ፍለጋ አንገትና ጆሮን እስስ መፈተሽ ይደርሳል። በዚህ ጊዜ ሁኔታቸውን የሚያስተውል ቢኖር ድርጊታቸው የፈጠነ እገዛ እንጂ የታሰበበት ዝርፊያ ላይመስለው ይችላል።
ይህ መሰሉ ጉዳይ በተነሳ ቁጥር መቼውንም የማልረሳው አንድ ታሪክ በአዕምሮዬ ይመላለሳል። ጊዜው ጥቂት ዓመታትን ወደ ኋላ ሳብ ይላል። ወቅቱ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ምርቃት የሚከናወንበት ነበርና በርካቶች ወደ ባሕርዳርና ጎንደር ለመጓዝ ከአዲስ አበባ መናኸሪያ ተገኝተዋል። እኔም የልቤ የምላትን የቅርብ ጓደኛዬን ለማስመረቅ ለጉዞ ተዘጋጅቻለሁ። አጋጣሚ መንገደኛው በርከት ቢል የአውቶቡሶቹ ቁጥር አነሰ። እንደታሰበው ትኬት አልተገኘምና ጥቂት ሰዓታት በፍለጋ ባከኑ።
አልረሳውም። ገና ክረምት መግባቱ ነበር። አየሩ ይቀዘቅዛል፣ ዝናቡ ያካፋል፣ ሰማዩም ጠቋቁሯል። ከቆይታ በኋላ አንድ መኪና ተገኘ ተብሎ ተሯሩጠን ወንበር ያዝን። ሁሉም ለጉዞ ዝግጁ ነበርና ሾፌሩ ግዜ አላባከነም። ከደቂቃዎች በኋላ መናኸሪያውን ለቆ ጉዞ ወደ ሱሉልታ አቅጣጫ ሆነ።
የኬላው ፍተሻ በአጭር ግዜ ተጠናቀቀ። ሾፌሩ የባከኑ ደቂቃዎችን ሊያካክስ በሚመስል ሁኔታ ፍጥነቱን ጨምሮ ተፈተለከ። አሁን የጎጃምን መንገድ ይዘናል። በአብዛኛው የተመራቂ ቤተሰቦችን ያሳፈሩ አውቶቡሶች ከኋላና ከፊት እየተፈተለኩ ያልፋሉ። ሁኔታቸው ውድድር እንዳለበት ያስታውቃል። በተለይ አንደኛው አውቶቡሰ አካሄዱ በእጅጉ ያስፈራል። ውስጡ ያሉ ተሳፋሪዎች በተከፈተላቸው ሙዚቃ እየጨፈሩ ነው። አውቶቡሱ እኛን ደርቦ እንደንፋስ ሽው ብሎ አለፈ።
ፍልቅልቅን ተሻግረን የዓባይ በረሃን መንገድ ጀምረናል። የግራቀኙ ገደልና የዓለት ተራሮችን ማየቱ እያስፈራን ነው። ጥቂት እንደተጓዝን መንገዳችን በመኪኖች መዘጋጋቱን አየን። ጉዳዩን ያወቅነው ዘግይተን ነበር። ከኋላችን እኛን ቀድሞ ያለፈው ፈጣኑ የመንገደኞች አውቶቡስ ሙሉ ተሳፋሪዎችን እንደያዘ በጥልቁ ገደል ወድቆ ተገልብጧል።
የአካባቢው አርሶአደሮች ለድረሱልን እርዳታ መሣሪያቸውን ይተኩሳሉ። ከገደሉ አፋፍ ጨኸቱ በርክቷል። እዚህም እዚያም በየጥሻው የወደቁ ሰዎች አብዛኞቹ በሕይወት አልነበሩም። ከመኪናው ጋር ቁልቁል ከተሽቀነጠሩ ተሳፋሪዎች ዘንድ አንዳች የሚሰማ ድምፅ የለም። በደቂቃ አፍታ የነበረው እንዳልነበረ ሆኗል። የዓባይ በረሀ ገደል፣ በዝምታ ተውጧል።
ከሌሎች መኪኖች የወረዱ መንገደኞች ገደል ውስጥ ወደገባው መኪና ለመድረስ ጢሻውን እየቧጠጡ ነው። ሙትና ቁስለኛን ለማንሳት ርብርቡ ቀጥሏል። ጥቂት ቆይቶ የብዙዎችን ዓይን የሳበ አንድ ወጣት ከገደሉ አፋፍ ብቅ አለ። በእጆቹ በርከት ያሉ የኪስ ቦርሳዎች፣ የእጅ ሰዓቶችና የወርቅ ሀብሎችን ይዟል። የራሱን መጫሚያ ጥሎ በሌላ አዲስ ጫማ ለመቀየሩ ምልክቶቹ ይመሰክራሉ።
ያዩት ሁሉ ወደእሱ አፍጥጠው ስለያዛቸው የበዙ ዕቃዎች እንዲያስረዳ ጠየቁት። መዋሸት አልቻለም። የእጁን ውድ ንብረቶች በሙሉ በአደጋው ከወደቁና በሕይወት ከሌሉ ሰዎች አንገት፣ እጅና ኪሶች ላይ እያማረጠ ስለመውሰዱ ተናገረ። ድርጊቱ ከማዘን በላይ በእጅጉ ያበሸቃቸው በቡጢና በርግጫ ተቀባበሉት። በመሐል አንድ ትልቅ ሰው ለግልግል ገብተው ለሕግ ተላልፎ እስኪሰጥ ዱላው ያለማቋረጥ መቀጠሉን አስታውሳለሁ።
እንዲህ አይነቶቹ ራስ ወዳዶች ባሉበት የድንገተኛ አደጋ አጋጣሚዎች ይበልጥ ይከፋሉ። ብዙዎች እርዳታ በሚያሻቸው ጊዜ ራሳቸውን ለመጥቀም ብቻ በሰው ቁስል የሚረማመዱ ክፉዎች በበረከቱ ቁጥር ሰው ይሉት ማንነት ትርጓሜው ይዛባል። ሰሞኑን በመዲናችን ትልቁ የገበያ ስፍራ መርካቶ መሐል የሆነውም እንዲሁ ነበር።
ምሽቱን በሸማ ተራ የገበያ ማዕከል የተነሳው ድንገቴ የእሳት ቃጠሎ በቀላሉ የሚቆጣጠሩት አልነበረም። በትንሹ መቀጣጠል የጀመረው እሳት እንደዋዛ ተስፋፍቶ በርካታ የንግድ ቤቶችን ከነሙሉ ንብረቶቻቸው አጋየ። ይህን አደጋ ለመታደግ በርካቶች ከያሉበት ተገኝተው ሲረባረቡ ታይተዋል።
በተቃራኒው ደግሞ ጥቂት የማይባሉ ራስ ወዳዶች በአመዱ ላይ ተራምደው ንብረት ሲዘርፉ፣ ኪሳቸውን ሲያደልቡ ብዙዎች አይተው ታዝበዋል። የንብረቶቹ በእሳት መጋየት ለእነሱ የጨለማ ብርሀን የሆነላቸው ክፉዎች በእጃቸው የገባን ዕቃ ያለምንም ይሉኝታ ሲያግዙና ሲቀባበሉት ነበር። ይህን ሲያደርጉ ደግሞ እንደራሳቸው መብት አንዳች ሳይሸማቀቁና ማንንም ሳይፈሩ ነው።
በተመሳሳይ ጎላ ሚካኤል በሚባለው ሰፈር ሰሞኑን በደረሰው የእሳት ቃጠሎ የተለመደው አሳፋሪ ድርጊት ተስተውሏል። አደጋውን ለመከላከል በሚመስል ቅርበት ስፍራው የደረሱ ልማደኛ ዘራፊዎች እንደ ጥሩ ዘመድ የተጎጂዎችን ንብረቶች እየተሸከሙ ከስፍራው እብስ ብለዋል።
የእሳት አደጋው የተነሳው ሌሊት ላይ ነበር። በተቃጠሉት ቤቶች ስጋት የገባቸው የአቅራቢያው ነዋሪዎች ንብረቶቻቸውን ማሸሽ ይዘዋል። ይህ እውነት አሳምሮ የገባቸው ልማደኞች ታዲያ አጋዥ ዘመድ መስለው ጉድ እንደሠሯቸው ተሰምቷል።
ወዳጆቼ! በተለያዩ አጋጣሚዎች ይህ መሰሉ ማንነት ሕጋዊ እየመሰለ ነው። እንደ አባባል ‹‹ግርግር ለሌባ ያመቻል›› ይሉት ተረክ ቢኖርም እንዲህ ሕሊናን በሚነጥቅ ደረጃ መስፋፋቱ ግን ከማሳዘን ባለፈ በእጅጉ ያሳፍራል። ብዙዎች የሚሉትን ቃል ልጠቀም። ‹‹ጎበዝ! ወዴት እየሄድን ነው ››?
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2017 ዓ.ም