በሠላምና አብሮነት ላይ ላተኮረው ዓለም አቀፍ ጉባኤ በቂ ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፡– ከጥቅምት 25 ጀምሮ ለሚካሄደው ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በቂ ዝግጅት መደረጉን የሠላም ሚኒስቴር አስታወቀ። ከተለያዩ ሀገራት የእምነት ተቋማት የመጡ እንግዶች በሚሳተፉበት ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሱ በሠላምና አብሮነት ጉዳዮች ላይ የልምድ ልውውጥ ይደረጋል።

በሠላም ሚኒስቴር የሠላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ከይረድን ተዘራ (ዶ/ር) ትናንትና በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ የሠላም ሚኒስቴር በዩናይትድ ዓረብ ኢሜሬት ከሚገኝ መሐመድ ቢን ዛይድ ዩኒቨርሲቲ ፎር ሂዩማኒቲ ከተባለ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከጥቅምት 25 ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳል።

ኢትዮጵያ በበይነ እምነቶች መካከል የሚደረግ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ለማካሄድ ዝግጅቷን አጠናቃለች ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ኮንፈረንሱ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይና ከሀገር ውስጥ ከአውሮፓ፣ ከእስያ፣ ከአፍሪካ እና ከተለያዩ የእምነት ተቋማት የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ 360 ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በሀገሪቱ በሃይማኖትና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠኑ 15 ታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሳተፉ ሲሆን፤ የኢትዮጵያን የሃይማኖት ተቋማት የአብሮነት እሴት የሚያሳዩ ጽሑፎች እንደሚቀርቡ አስታውቀዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ በጉባኤው የእምነት ተቋማት በሠላምና በአብሮነት ጉዳዮች እየሠሩ ያሉትን ሥራዎች በተመለከተ ውይይት ይደረጋል። በጉባኤው የሚሳተፉ ሀገራትም ልምድና ተሞክሯቸውን ያካፍላሉ፡፡

በአጠቃላይ በጉባኤው የእምነት ተቋማት ተሳታፊዎች አብረው መሥራት የሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል። አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች በርካታ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኝ ገልጸው፤ የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች የአንድነት ፓርክን፣ የዓድዋ ሙዚየምን፣ የኮሪደር ልማቶችን እንደሚጎበኙ አስታውቀዋል።

እንግዶቹ በኢትዮጵያ በእምነት ተቋማት መካከል ያለውን አብሮነት እንደሚመለከቱ ይደረጋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ታላላቅ አሕጉራዊና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን ማዘጋጀት የምትችል ሀገር መሆኗን እንዲሁም የአብሮነትና የመቻቻል ተምሳሌት መሆኗን የምታሳይበት መድረክ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ እምነቶችን እንደ ዓለም ቅርስነት ከመጠበቅ አልፋ ለዓለም የሥልጣኔ መገለጫ እና መታያ እያደረገች መሆኗ ጉባኤውን እንዲታዘጋጅ ዋና መነሻ ሆኗል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ የእምነት ተቋማት በሀገር፣ በሠላም እና በትውልድ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህን አበርክቷቸውን እንዲያጠናክሩም ጥሪ አቅርበዋል።

በጉባኤው መክፈቻ ዕለት የኢትዮጵያን የእምነት ተቋማት አብሮነት የሚያሳይ የፎቶግራፍ ዓውደ ርዕይ በሀገሪቱ ከፍተኛ አመራሮች እንደሚከፈት አመላክተዋል፡፡

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You