የዘመነ አገልግሎትን የሚሻው የቱሪዝም ዘርፉ

በጦርነት፣ በኮቪድ ወረርሽኝና በሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት የተጎዳው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ማንሰራራት መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መግለጣቸው የሚታወስ ነው። መንግሥትም የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምሰሶዎች አንዱ አድርጎ የቱሪዝም ዘርፉ ላይ በስፋት እየሠራበት ይገኛል።

ቱሪዝም ራሱን ችሎ በሚኒስትር ደረጃ እንዲቋቋም ከማድረግ አንስቶ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ተደራሽ እስከማድረግ የደረሱ በርካታ ውጤታማ ሥራዎች ከለውጡ በኋላ ተከናውነዋል።

በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ሀገርና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች በተለያዩ ክልሎች በርካታ ቱሪስቶችን መሳብ የሚችሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተገንብተዋል፤ እየተገነቡም ነው። መሰል የመሠረተ ልማት ሥራዎች ቱሪዝሙን ለማሳደግ አይነተኛ ሚና እንዳላቸው እሙን ነው። ይሁንና ከቱሪዝም ልማቱ ጋር ተያይዞ የሠለጠነ የሰው ኃይልና የዘመነ አገልግሎት ደግሞ አስፈላጊ መሆኑን ባለሙያዎችና የዘርፉ ኃላፊዎች ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

የሆቴልና ቱሪዝም ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አሸናፊ ሙሉጌታ እንደሚናገሩት፤ ታይላንድና የተለያዩ ሀገራት ያላቸውን አነስተኛ ነገር ይዘው በሠለጠነ መንገድ አገልግሎት ስለሚያቀርቡ የቱሪዝም ገቢያቸው አያሌ መሆኑን ይጠቁማሉ።

ኢትዮጵያ በቂ የቱሪዝም ሃብት እያላት የመሠረተ ልማት ግንባታውም እያደገ የዘመነ አገልግሎትን በተሻለ መንገድ ማቅረብ ባለመቻሉ የሚደርሰውን ኪሳራ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ኪሳራውን ለማካካስ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ ሀገራት ጭምር ሥልጠናና በማቅረብ እንዲሁም ልምዶችን በመቅሰም የቱሪዝም አገልግሎት ዘርፉን ማዘመን ይገባል ሲሉ ያስረዳሉ።

በዘርፉ ያለውን አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን ሆቴሎችን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መገንባትና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን ማሰማራት እንዳለባቸው ይጠቁማሉ።

እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን አቅም መገንባት ለሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት አይነተኛ ሚና አለው፡፡ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ ላይ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ተከታታይ ሥልጠና በዘላቂነት ማቅረብ ያስፈልጋል።

በሆቴልና ቱሪዝም እንዲሁም በባሕላዊ ሆቴሎች ዙሪያ የሚጠበቀውን ያህል እድገት እንዳልተመዘገበ የሚናገሩት አቶ አሸናፊ፤ በዘርፉ የሚሰጡትን አገልግሎቶች አንድ ርምጃ ወደፊት በማስኬድ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ ይገባል ይላሉ።

አዲስ አበባ በቱሪዝም መስክ ውጤታማነቷን እያሳደገች ነው በቀጣይ ደግሞ አገልግሎቱም ላይ ትኩረት ተደርጓል ያሉት ደግም የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ናቸው፡፡

እንደእርሳቸው ከሆነ፤ ቱሪዝም ፈጣን ቀልጣፋና የዘመነ አገልግሎትን ይሻል። አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ብቻ ሳይሆን ለቱሪዝም ዘርፉ ምቹ ለማድረግ በርካታ መሠረተ ልማቶች ተገንብተዋል። ነገር ግን በቀጣይ በትልቁ ትኩረት ሰጥቶ መሠራት ያለበት ፈጣን፣ ቀልጣፋና የዘመነ አገልግሎት ላይ ነው፡፡

በጣም ቅን የሆነና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት የምንሰጥበትን ሁኔታዎች ካልፈጠርን መሠረተ ልማት ብቻውን ቱሪዝምን እንደማያሳድግ አቶ ሞገስ ያነሳሉ። የሆቴልና ቱሪዝም ተቋማት፣ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ የወጣቶችና ከኪነጥበብ ባለሙያዎች እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፉ የሚሠሩ ባለድርሻ አካላት መሠረተ ልማቱ ላይ ተመሥርቶ አገልግሎት አሰጣጡን የማዘመን፣ ለተገልጋዮች ምቹና ሠላማዊ ማድረግ ላይ በቀጣይነት አፅንዖት ሊሰጡት ይገባል ይላሉ።

ሀገራችን ቱባ የሆኑ ባሕላዊ ቅርሶችና ሀብቶች ያላት ሆና በተለያዩ ግጭቶችና አለመግባባቶች ምክንያት ችግር ይፈጠራል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች የሚመጣውም ቱሪስት እየሰፋ እንዲሄድ ጥራት ያለው አገልግሎትን በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ መሥራት ይገባል ሲሉ ነው ያመላከቱት።

የአዲስ አበባ ባሕል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሒሩት ካሣው (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ቱሪዝም ከጉብኝትና ከተለያዩ የመዝናኛ እንቅስቃሴዎች ባለፈ ከተለያየ አስተዳደግ፣ አኗኗር፣ እምነትና ባሕል የመጡ ሰዎችን የሚያገናኝ ድልድይ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

የዘርፉ ተዋንያን የመንግሥት የግሉ ዘርፍና የሲቪክ ማኅበራት በመሪነት አንድ ላይ በመሆን እያንዳንዱን የውጪም ሆነ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንቅስቃሴን ወደ ሀገር ግንባታ እንዲቀየር በመልካም ሥነምግባርና በዘመነ አገልግሎት ማገልገል እንደሚገባም ይገልጻሉ።

ሀገር በቱሪዝም ስታድግ እንደግለሰብም ገቢ ሊያድግ እንደሚችል በማሰብ አስጎብኚዎች፣ የቱሪዝምና ሆቴል ተቋማትና ባለሙያዎችም እራሳቸውን ለማስተማር፣ አገልግሎታቸውን ለማሻሻልና ብቃት ያለው መስተንግዶ ለማቅረብ ከወዲሁ አስበው ሊሰሩ እንደሚገባም ያስገነዝባሉ።

ቱሪዝም ከመሠረተ ልማት ባሻገር ብቁ ባለሙያና ምቹ አገልግሎትን ስለሚሻ እያንዳንዱ ግለሰብ ዘመኑን የዋጀ አገልግሎትን በማቅረብ ጥረት ማድረግ እንዳለባት ባለሙያውና ኃላፊዎቹ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

ነፃነት ዓለሙ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You