አዲስ አበባ፦ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው ዓለም አቀፍ የግብርና ዓውደ ርዕይ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የንግድ ግንኙነትን ለማጠናከር አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ዓለም አቀፍ የግብርና ዓውደ ርዕዩ ትናንት በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ተከፍቷል።
በወቅቱ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ዓውደ ርዕዩ የገበያ ትስስር ለመፍጠር፣ የቴክኖሎጂና ልምድ ልውውጥ የኢትዮጵያን አቅም ለዓለም ለማሳየት ያግዛል።
ዓውደ ርዕዩ ኢትዮጵያ ያላትን አቅም ለማስተዋወቅና ዘርፉ ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ለሚያፈሱ በሀገር ውስጥ ያለውን ምቹ ሁኔታ ለማስተዋወቅ ይረዳል ብለዋል።
ዘርፉ ላይ የተሠማሩ ድርጅቶችም የልምድ ልውውጥ እንዲያገኙና በቀጣይነትም አብሮ ለመሥራት የሚያስችል የንግድ ግንኙነት እንዲፈጥሩ መልካም ዕድል አግኝተዋል ሲሉ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ሰፊ የእንስሳት ሀብት ያላት ሀገር ናት ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ዘርፉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና አሠራር ባለመደገፉ፣ በእውቀት ባለመመራቱና አስቻይ ፖሊሲዎች ባለመኖራቸው የሚፈለገውን ያህል ጥቅም ሳያስገኝ መቆየቱን አስታውሰዋል።
አሁን ላይ የፖሊሲ ማሻሻያን ጨምሮ የዘርፉን ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፤ ባለፉት ዓመታት እየተተገበረ በሚገኘው የልማት ትርፋትም ከፍተኛ ውጤት ማስገኘቱን ገልጸዋል።
የመንግሥት፣ የግሉ ዘርፍና ሌሎችም ባለድር ሻዎች ትብብር የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ እንደሚረዳ ጠቅሰው፤ ይህን መሰል ዓውደ ርዕዮችም የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የገበያ ዕድልና አብሮ የመሥራትን ዕድል ይፈጥራሉ ብለዋል። ይህም ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የገጠሩን ማኅበረሰብ ኑሮ ለማሻሻል የያዘችውን ትልም እውን ለማድረግ ያግዛል ሲሉ አንስተዋል።
በኢትዮጵያ በግብርናና እንስሳት ልማት ለመሠማራት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረው፤ በቅርቡ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በተለይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ወጪ ንግድን ለማበረታታት እንደ ሚያግዝ ጠቁመ ዋል።
በቀጣይ የውጪም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በእንስሳት ሃብት ልማት በመሳተፍ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።
የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አሥራት ጤራ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዓውደ ርዕዩ የሀገር ውስጥ አምራቶች የገበያ መዳረሻ እንዲያገኙ፣ የግብዓት አቅርቦት ትስስር ለመፍጠር እንዲሁም የውጭ ባለሀብቶችን ወደሀገራችን ለመሳብ ያስችላል ብለዋል።
የገበያ ትስስሩ የተጀመረውን የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ተጨማሪ እቅም ይፈጥራል ሲሉ ተናግረዋል።
የዓውደ ርዕዩ አስተባባሪና የፕራና ኢቨንት ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ለማ ፤ በዓውደ ርዕዩ ከ14 ሀገራት የተውጣጡ ከ100 በላይ ዓለም አቀፍ የእንስሳት ሃብት ዘርፍ ተዋናዮች ተሳታፊ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም