አዲስ አበባ፡– ረሃብን ለመቀነስ ታሳቢ ተደርጎ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የመፍትሔ ሃሳቦችን ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገለጸ።
በተባበሩት መንግሥታት ኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት አዘጋጅነት “ረሀብ አልባ ዓለምን መፍጠር ይቻላል” በሚል ርዕስ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በኢትዮጵያ ሊካሄድ መሆኑ ተገልጿል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር መላኩ አለበል እንደገለጹት፤ ከጥቅምት 26 ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆይ ዓለም አቀፍ ኮንፈረስ በአዲስ አበባ በዓድዋ ሙዚየም ይካሄዳል።
በኮንፈረንሱ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት እንዲሁም የዓለም የምግብ ድርጅት በአዘጋጅነት የሚሳተፉ ሲሆን ከአንድ ሺህ 500 በላይ ባለድርሻ አካላት ይሳተፋሉ። ከነዚህም ውስጥ 800 የሚሆኑት ከውጭ ሀገራት የሚመጡ ናቸው ብለዋል።
በኮንፈረሱ ዘላቂ የቴክኖሎጂ አማራጮችን በመጠቀም ረሀብን እንዴት መዋጋት እንደሚቻል፤ የረሀብን ችግር ለመፍታት መንግሥትና የግል ሴክተሩ በምን መልኩ መሥራት እንዳለባቸው እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የልማት አጋሮችን እንዴት ማስተባበር ይቻላል በሚለው ዙሪያ ውይይት እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
ይህም የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ ችግርን በዘላቂነት ሊፈቱ የሚችሉ የመፍትሔ ሐሳቦችን ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሚኒስትሩ አመላክተዋል።
ይህ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በኢትዮጵያ መዘጋጀቱ በርካታ ጠቀሜታዎች እንደሚኖሩት የገለጹት አቶ መላኩ፤ በተለይም በግብርና፣ ኢንዱስትሪ እና ቱሪዝም ዘርፍ የተገኙ ስኬቶችን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የምታስተዋውቅበት ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል ።
የተባበሩት መንግሥታት ኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ተወካይ ደጀኔ ተዘራ በበኩላቸው፤ ዓለምን ብሎም አፍሪካን እየፈተነ ያለው የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለከፋ ችግር እና እንግልት እየዳረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ11 ሰው አንዱ በረሀብ የሚጠቃ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ደጀኔ፤ በአፍሪካ ደግሞ ከአምስት ሰው አንዱ ይራባል ብለዋል።
በዚህ ኮንፈረንስ የሀገራት መሪዎች፣ የቴክኖሎጂ ተቋማት፣ ምሑራን፣ የግል ሴክተሮች እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የገሀብ ተጋላጭነት እንዴት መቀነስ ይቻላል በሚለው ዙሪያ የሚመክሩ መሆኑን አስታውቀዋል።
አቶ ደጀኔ የዓለም የምግብ ዋስትና ችግርን ለመፍታት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸው፤ ጉባዔው ይህንን ለማስገንዘብ የሚካሄድ መሆኑን አስታውቀዋል።
መስከረም ሰይፉ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም