በሦስት ወራት 95 ሺህ ዩኒት ደም ተለግሷል

አዲስ አበባ፡– በ2017 በጀት ዓመት በሩብ ዓመቱ 95 ሺህ ዩኒት ደም ማሰባሰብ መቻሉን የኢትዮጵያ ደምና ኅብረሕዋስ ባንክ አገልግሎት አስታወቀ። ከተሰበሰበው ደም 29 ሺህ ዩኒት ከአዲስ አበባ መገኘቱም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ደምና ኅብረሕዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ሦስት ወራት 95 ሺህ ዩኒት ደም ማሰባሰብ ተችሏል።

በመጀመሪያ ሩብ ዓመት 100 ሺህ ዩኒት ደም ለማሰባሰብ ታቅዶ 95 ሺህ ዩኒት ደም ማሰባሰብ ተችሏል ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ የደም ማሰባሰብ መርሐግብሩ ከክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጋር በማስተሳሰር እና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማደራጀት ማሰባሰብ ተችሏል ብለዋል።

በአጠቃላይ ከተሰበሰበው 95 ሺህ ዩኒት ደም ውስጥ 29 ሺህ ዩኒት የሚሆነው ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መሰብሰቡን ጠቅሰው፤ የክረምት መርሐ ግብሩ ካለፉት ጊዜያት የተሻለ ውጤት የተገኘበት መሆኑን ገልጸዋል።

ደም ልገሳ በሰዎች መልካም ፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን የሚገልጹት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ መርሐግብሩ መንግሥት ያወጀው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል ሆኖ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል ብለዋል።

ትምህርት መጀመሩን ተከትሎ በትምህርት ቤቶች ላይ ለሚሰበሰበው ደም የመምህራን አስተዋፅዖ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ ትምህርት ቤቶች የደም ልገሳውን በባለቤትነት እንዲያግዙ የሚያስችል መግባባት መፍጠር መቻሉን ተናግረ ዋል።

በትምህርት ቤቶች በሚደረገው የደም ማሰባሰብ ሂደት ላይ አብዛኞቹ ተማሪዎች የክብደት መጠናቸው ከ45 እስከ 50 ስለሆነ አንድ ዩኒት ደም ብቻ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ክብደታቸው ከ50 በላይ ከሆኑ ሰዎች 450 ሚሊ ሊትር በመሆኑ የደም ተዋፅዖ የሚወጣለት ደም በብዛት እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በሃይማኖት ተቋማት በበዓላት ቀን ላይ የደም ማሰባሰብ ሥራ እንደሚሠራ በመግለጽ፤ ተቋማቱም በደም ማሰባሰብ ሂደት ላይ የራሳቸውን አስዋተፅዖ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በደም ልገሳ በኩል በማኅበረሰቡ ዘንድ መነቃቃት የተፈጠረ ቢሆንም በአማራ ክልል ያለው የፀጥታ ሁኔታ ወረዳዎች ላይ ደም ለማሰባሰብ መቸገራቸውን የገለጹት አቶ ሀብታሙ፤ በክልሉ በሚገኙ የደሴ፣ ደብረብርሃንና ባሕርዳር የደም ማሰባሰቢያ ባንኮች ደም እየተሰበሰበ ይገኛል ብለዋል።

ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ደም እየተገኘ ቢሆንም ትላልቅ ሰዎች ሲለግሱ የተሻለ የደም ተዋፅዖ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ኅብረተሰቡ የደም ልገሳውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።

የተለገሰው ደም የጥንቃቄ ሥራ ሂደትን ተከትሎ ከተለገሰበት ቦታ ወደ ደም ባንክ እንዲመጣ የሚደረግ መሆኑን በመግለጽ፤ የደሙን ደኅንነት ለማረጋገጥ ምርመራ እንደሚደረግና የደም ዓይነት ልየታ ከተደረገ በኋላ ነፃ የሆነ ደም ለስርጭት እንደሚቀርብ አስረድተዋል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ዓርብ ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You