በዓለም አቀፍ የሁዋዌይ አይሲቲ ውድድር ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተሸለሙ

አዲስ አበባ፡በዓለም አቀፍ የሁዋዌይ አይሲቲ ውድድር ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ኢትዮጵያውያን ተሸላሚ ሆነዋል።

ሁዋዌይ “Huawei ICT Competition 2023-2024” ላይ ጥሩ ውጤት ላመጡ ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች እውቅና እና ሽልማት በትናንትናው ዕለት አበርክቷል። የ2024-2025 ውድድር መርሐ ግብርም ይፋ አድርጓል ።

በወቅቱ ንግግር ያደረጉት የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተወካይ ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ውድድሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ የአይሲቲ ሥነምሕዳር ለማዳበር ያለውን ቁርጠኝነት ያጎላል።

በትምህርትና በኢንዱስትሪ መካከል ያለውን ልዩነት በማጥበብ ትውልዱ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን ፈጣሪም እንዲሆን የሚያደርግ ነውም ብለዋል።

ተሸላሚዎች ቴክኖሎጂ ላይ ያላቸውን ፍላጎት በማሳደግ ለኅብረተሰቡ እድገት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ማበርከት እንደሚኖርባቸው ያሳሰቡት ተወካዩ፤ ተሸላሚዎቹ ላይ ያለው የቴክኖሎጂ እውቀት የሀገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፋንታ ላይ ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።

እንደ ሁዋዌይ አይሲቲ ውድድር ያሉ ውጥኖች የግድ አስፈላጊ መሆናቸውን የጠቀሱት ስሜነው (ዶ/ር)፤ ለወጣቱ አዕምሯዊ እድገትን የቡድን ሥራን፣ ችግር ፈቺ ፈጠራዎችን እንዲሠራ ያደርጋል ሲሉ አብራርተዋል።

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በ2023-2024 የአይ.ሲ.ቲ ውድድር የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኢትዮጵያን ወክለው በዓለም አቀፍ መድረክ በቻይና ሼንዘን ሦስተኛ ደረጃን አግኝተዋል። ይህ አስደናቂ ውጤት ነው ብለዋል።

ከHuawei ያገኙትን ደረጃውን የጠበቀ ዓለም አቀፍ ሥልጠና ለዚህ ውጤት መምጣት ዋነኛው ነገር ነው ብለዋል።

የሁዋዌይ ኢትዮጵያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ላይሚን፤ ውድድሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአይ.ሲ.ቲ ላይ እውቀት ያላቸው ዜጎችን ከተወዳደሩ በኋላ የተደረገ ዓለም አቀፍ ውድድር መሆኑን ተናግረዋል።

የተሸለሙት ተወዳዳሪዎች በ8ኛው ዙር ውድድር በተለያዩ ዘርፎች ከዓለም ተወዳዳሪዎች ውስጥ ሦስተኛ ደረጃ የያዙ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

መድረኩ ከውድድር ባለፈ የሥራ ዕድልን፣ የእውቀት ሽግግርን እንዲሁም ተቋማዊ ግንኙነቶችን የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

ሽልማቱ በመላ ሃገሪቱ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ከተውጣጡ ሁለት ሺህ 500 ተማሪዎች የተሻለ ብቃት በማሳየትና ፈተና በማለፍ በቻይና በተካሄደው ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ሦስተኛ ደረጃን የያዙ ዘጠኝ ተወዳዳሪዎች ማበርከቱ በመድረኩ ገልጸዋል።

በ9ኛው ዙር የHuawei አይ.ሲ.ቲ ወድድርም መስፈርቱን ያሟሉ ተወዳዳሪዎች ቀጣናዊ ውድድር ካደረጉ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወዳደሩ መሆኑ ጠቁመዋል ።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You