ኬሚካሎችን በጥራት በማዘጋጀት የኢንዱስትሪዎችን ግብዓት ለማሟላት ትኩረት ተሰጥቷል

አዲስ አበባ:- በኢትዮጵያ የተለያዩ የኬሚካል ምርቶችን በጥራት በማዘጋጀት የኢንዱስትሪ ዘርፉን ግብዓት ለማሟላት ትኩረት ተሰጥቷል ሲሉ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ሐድጉ ኃይለኪሮስ (ዶ/ር) ተናገሩ።

በኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን የአዋሽ መልካሳ ኬሚካል ፋብሪካ ኃላፊዎች ከደንበኞችና ከሚመለ ከታቸው አካላት ጋር ትናንትና ምክክር አድርገዋል።

በውይይቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ሐድጉ ኃይለኪሮስ (ዶ/ር)፤ በሀገር ደረጃ የተለያዩ የኬሚካል ምርቶች በጥራት በማምረት የማኑፋክቸሪንግና የኢንዱስትሪ ዘርፉን ከማሳደግ በተጨማሪ የሀገሪቱን የውጪ ምንዛሪ እጥረት የመተካት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል ።

ለማኑፋክቸሪንግና ለኢንዱስትሪ እድገት ቁልፍ ሚና የሚጫወተውን የኬሚካል ምርት በሀገር ውስጥ በጥራት በማምረት፤ በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ በማድረግ ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።

መንግሥት በሀገሪቱ ሁለተናዊ እድገት በማስ መዝገብ ብልፅግናን እውን ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራባቸው ካሉ ሥራዎች አንዱ በውጪ የሚመረቱ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች የመተካት ሥራ ነው ብለዋል።

ተኪ ምርቶችን የማምረት ተግባር ዋናው የሥራችን አካል ነው ያሉት ሐድጉ (ዶ/ር)፤ የኬሚካል ምርቶችንም በሀገር ውስጥ በማምረት ኢንዱስትሪውን የማሳደግና የውጪ ምንዛሪ ወጪን የመቀነስ ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ሀገራዊ እድገትን እውን ለማድረግ የተኪ ምርቶችን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ተገቢ ነው፤ በኬሚካል ኢንዱስትሪዎች ላይ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎችን በመዘርጋትና በማበረታት በኩል ውጤታማ ሥራ እያከናወነ ይገኛል ሲሉ አንስተዋል። የኬሚካል ምርቶችን በጥራት በማምረትና በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ ሥራ ከግሉ ዘርፍ ተዋንያን ጋር በትብብር የሚሠራ መሆኑን አመላክተዋል።

የኬሚካል ምርቶችን በሀገር ውስጥ በጥራት መመረታቸውም የውጪ ምንዛሪን ወጪን ከመቀነስ ባለፈ ለሥራ አጥ ዜጎችም የሥራ ዕድል እየፈጠረ ነው ብለዋል።

ከውጪ የሚገቡ የኬሚካል ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት መንግሥት ለኬሚካል ኢንዱስትሪው ትኩረት ከመስጠት በተጨማሪ ኢንቨስትመንትን የማሳደግ ውጥኑን ለማሳካት እንደሚያግዘው ገልጸዋል።

አዋሽ መልካሳ የኬሚካል ፋብሪካ የተለያዩ የኬሚካል ምርቶችን በጥራት በማምረት ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው እንዲያድግ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ አራጌ በበኩላቸው፤ የኬሚካል ምርትን በጥራት በማምረት በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው።

የኬሚካል ምርት ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት የጀርባ አጥንት ነው፤ አዋሽ መልካሳ የኬሚካል ፋብሪካ ጥራት ያለው ኬሚካል በማምረት በሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።

ተቋሙ ሚናውን ይበልጥ ለማሳደግ በቴክኖሎጂና በፈጠራ የማስደገፍ ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ የተናገሩት ደግሞ አዋሽ መልካሳ የኬሚካል ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሕመድ ሞቱማ ናቸው።

ፋብሪካው በሰሜኑ ጦርነትና በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ኪሳራ ገጥሞት እንደነበር አስታውሰው፤ ከአመራር እስከ ሠራተኛ በቅንጅት በመሥራት ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ ተሠርቷል ሲሉ ተናግረዋል።

ፋብሪካው የተትረፈረፈ የኬሚካል ምርት እያመረተ ቢሆንም በሚፈለገው ልክ ገበያ ያለማግኘት ችግር በመኖሩ ገበያ ልማት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You