በመዲናዋ በሩብ ዓመቱ ለ36 ሺህ 141 ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል

አዲስ አበባ፦ በመዲናዋ በሩብ ዓመቱ ለ36 ሺህ 141 ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የአዲስ አበባ ከተማ ሥራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ። በታኅሣሥ ወር የ”ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ” ፕሮግራም ምዝገባ ይከናወናል።

በቢሮው የሥራ ስምሪት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ሰብሃዲን ሡልጣን ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በ2017 በጀት ዓመት 300 ሺህ ለሚሆኑ ነዋሪዎች ቋሚ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዷል። ከዚህ ውስጥ በሩብ ዓመቱ ለ45 ሺህ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ36 ሺህ 141 ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።

የተፈጠረው የሥራ ዕድል በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በከተማ ግብርና፣ በአገልግሎትና ተያያዥ ዘርፎች መሆኑን ጠቁመው፤ በተያዘው በጀት ዓመት ከ10 ሺህ 500 በላይ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ለመፍጠር ታቅዶ በሩብ ዓመቱ አንድ ሺህ 361 ኢንተርፕራይዞችን መፍጠር ተችሏል ብለዋል።

ቢሮው ለነዋሪዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በኢንተርፕራይዞች፣ በድርጅቶች እና በመንግሥት በተያዙ ፕሮጀክቶች ያሉ ክፍት የሥራ ቦታዎችን የማፈላለግ ሥራ እንደሚሠራ ገልጸው፤ በዚህም ከ195 ሺህ በላይ የሚሆኑ ክፍት የሥራ መደቦች መለየት ተችሏል። በቦታዎቹም ነዋሪዎች የሥራ ዕድል እንዲኖራቸው ይደረጋል ሲሉ አስረድተዋል።

አሁን ላይ ገበያ ተኮር የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ተደርጓል ያሉት አቶ ሰብሃዲን፤ በሥራ ፈላጊዎች ዘንድ ግን ሥራና ደመወዝ የማማረጥ እንዲሁም ቀኑን ሙሉ ለመሥራት የፍላጎት ማነስ እንደሚስተዋል ተናግረዋል።

በታኅሣሥ ወር የ”ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ” ፕሮግራም ምዝገባ ይከናወናል። በዚህም 15 ሺህ ወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ያደርጋሉ ያሉት አቶ ሰብሃዲን፤ ፕሮግራሙ በ2015 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በሁለት ዙር ከሃያ ሦስት ሺህ በላይ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

በዚህም በርካቶች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ገልጸው፤ በታኅሣሥ ወር የሚደረገው ምዝገባ ሦስተኛው ዙር እንደሆነ አመላክተዋል። በአሁኑ ወቅት ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎች እና የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ አቶ ሰብሃዲን ከሆነ፤ በሀገሪቱ በየዓመቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት ወደ ሥራ ገበያው ይቀላቀላል። በቀጣይም ወጣቶችን መደገፍና ሥራ የሚፈጥሩ የግል ባለሃብቶችን ማበረታታት ያስፈልጋል።

በተለይም በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት ትምህርታቸውን በዩኒቨርሲቲ፣ በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ገብተው መማር ያልቻሉ ወጣቶችን የሚያግዝ ፕሮጀክት ተቀርፆ ወደ ሥራ መገባቱ ለተያዘው ለዜጎች ሥራ ዕድል የማመቻቸት ትግበራ አጋዥ መሆኑን አቶ ሰብሃዲን ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ ለሚኖሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለማመቻቸትና ከግሉ ዘርፍ ጋር ለማስተሳሰር እየተሠራ ያለው ሥራ ውጤታማ እንደሆነም ተናግረዋል።  “ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ” ፕሮግራም በ2018 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ታውቋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You