አዲስ አበባ፡– ሠላማዊ በሆነ መንገድ በቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር በማግኘት ረገድ ኢትዮጵያ ወደኋላ የማይል ይፋዊ አቋም እንዳላት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሳወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትላንት በተካሄደው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከሕዝብ ተወካዮች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ የማይናወጥ ብሔራዊ ጥቅም አላት ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሠላማዊ በሆነ መንገድ በቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር ያስፈልጋታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሀገሪቷ በዚህ ጉዳይ ወደኋላ የማይል ይፋዊ አቋም እንዳላት አሳውቀዋል፡፡ ይህን ለማሳካት ጦርነትም ሆነ የኃይል አማራጭ አንፈልግም ብለውም፤ ፍላጎቷን ለማሳካት ኢትዮጵያ ሠላማዊ አማራጭን እንደምትከተል ገልጸዋል፡፡
የባሕር በር ማግኘት ምክንያታዊና ፍትሐዊ ጥያቄ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይንን “እኛ ባናሳካው ልጆቻችን ያሳኩታል” ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የትኛውንም ሀገር ላይ ወረራም ሆነ ጥቃት እንደማትፈጽም፤ ነገር ግን ኢትዮጵያን ለመንካት የሚሞክሩ ካሉ አሳፍሮ መመለስ የሚያስችል በቂ አቅም እንዳለ ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ አቋም ከሁሉም ጋር በትብብርና ሰጥቶ በመቀበል መርሕ መኖር ነው። ኢትዮጵያ የአፍሪካ የኃይል ማዕከል ናት፤ ከራሷ ባለፈ ለአፍሪካ ልማት ቁርጠኛ ናት።
ኢትዮጵያ ከየትኛውም ጎራ ጋር ሳትሰለፍ ከሁሉም ጋር በሰጥቶ መቀበል መርሕ ለብሔራዊ ጥቅሟ መሥራት እንደምትቀጥል በመግለፅ፤ ለኢትዮጵያ ሕልም ከሚመች የትኛውም ሀገር ጋር በትብብር ይሠራል ብለዋል። በተለይ በአሁን ወቅት ብሔራዊ ጥቅምን ባስከበረ መልኩ ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋር በትብብር እየተሠራ እንዳለ አመላክ ተዋል።
ሠላም ወዳድና የጋራ ሕልም ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሀገርን ከሰፈር በላይ አድርገው ማሰብ ከቻሉ ማንም አካል ኢትዮጵያን በኃይል ማንበርከክ እንደማይችልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
እንታገላለን የሚሉ ኃይሎች ከጠላት ጋር እየሠሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የጠላት መሣሪያ ከመሆን መቆጠብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ውስጣዊ አንድነትና ሠላም ለዲፕሎማሲያዊ ጥንካሬ ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህን አስቀድሞ መሥራት አለበት ብለዋል።
ከሶማሌያ ጋር ተያይዞ በሚነሱ ጉዳዮች ኢትዮጵያ ከሶማሌያ ጋር ምንም አይነት አሉታዊ አጀንዳ እንደሌላት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አጀንዳ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ መሆኑን በመግለጽ፤ ይህንን የማስገንዘቡ ሥራ እየተሠራ እንዳለ ጠቅሰዋል። በዚህ ረገድ ከየትኛውም ሀገር ጋር ለኢትዮጵያ የሚያዋጣው ሠላማዊ ጉርብትና መሆኑንም አንስተዋል። በሰጥቶ መቀበል አብሮ ማደግ እንዲሚገባም ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያን አክብሮና ጉርብትናዋን ወዶ መኖር፤ ጥቅሟን ያለ ምዝበራ መጋራት እንጂ ከእንግዲህ በኋላ ኢትዮጵያውያንን እያባሉ መኖር የማይቻል ነው ብለዋል።
“አርበኞች እንጂ የሌላውን አጀንዳ የምናራግብ ቅጥረኞች አይደለንም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ይህንን አምነው ከሚያከብሩ ሀገራት ጋር በጋራ ለመስራት ፍላጎቱ እንዳለ ተናግረዋል።
ይህንን አስታኮ ውጊያ ይነሳል ብለው ለሚሰጉ አካላት ኢትዮጵያ የመዋጋት ፍላጎት እንደሌላት አስረድተዋል።
በሌላ በኩል አንዳንድ ሀገራት ኢትዮጵያን ሊወሩ ይችላሉ የሚል ስጋት በአንዳንድ አካላት እንደሚነሳ ጠቁመው፤ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያን ማንም በኃይል መውረር እንደማይችል አስታውቀዋል።
ለመመከት የሚያስችል በቂ አቅም እንዳለም ተናግረዋል። “ማንም ላይ ጦር የመስበቅ ፍላጎት የለንም፤ ማንም ኢትዮጵያን እንዲደፍር ግን አንፈቅ ድም” ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም
አዲሱ ገረመው