– ፍራንኮ ቫሉታ በቅርቡ ማስተካከያ እንደሚደረግበት ተጠቅሷል
– በባንክ ስም የሚዘርፉ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተገልጿል
አዲስ አበባ:- የሪፎርም ሥራዎች በአብዛኛው የተጠናቀቁ በመሆኑ የተያዘው 2017 ዓ.ም የማንሰራራት ዓመት እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍራንኮ ቫሉታ በቅርቡ ማስተካከያ እንደሚደረግበት፤ በባንክ ስም የሚዘርፉ አካላት ላይ ክትትል እና እርምጃ እንደሚወሰድ እና አንዳንድ ኤምባሲዎች ከዘረፋ እና የውጭ ምንዛሪ ቢዝነስ እንዲታቀቡ አሳስበዋል።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፤ አብዛኞቹ የሪፎርም ሥራዎች የተጠናቀቁ በመሆናቸው ‹‹ዘንድሮ ሀገራዊ ማንሠራራት የምንጀምርበት ዓመት ይሆናል›› ብለዋል።
ባለፉት ስድስት ዓመታት እየተከናወኑ የመጡ ሪፎርሞች ተጠናቅቀው በታሪክ ታይተው የማይታወቁ ውጤቶች እየታዩ ለትውልድ የማፅናት ሥራ የሚጀመርበት ዘመን መጀመሪያ ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል።
በፍራንኮ ቫሉታ የተገኘው ውጤት ከዚህ በላይ መሸከም ተገቢ እንዳልሆነ የሚያሳይ በመሆኑ ማስተካከያ እንደሚደረግበትም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያን ሃብት በመዝረፍ እና የውጭ ምንዛሪ ቢዝነስ ላይ የተሰማሩ አንዳንድ ኤምባሲዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም አሳስበዋል።
በፍራንኮ ቫሉታ ስም የተለያዩ ኩባንያዎች በወርቅ ንግድ የኢትዮጵያን ገበያ የሚያዛቡ መኖራቸውንና ዓላማውን ስቶ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሃብት ማሸሻ እየሆነ በመምጣቱ እርማት ማድረግ ማስፈለጉን ተናግረዋል።
ሹፌሮች፣ ትናንሽ ሥራ የሚሠሩ ሳይቀሩ በኢትዮጵያ ብላክ ማርኬት ዶላር ወደ አንዳንድ ሀገራት በባቡርና በቅጥቅጥ መኪና እንደሚያስወጡ በመግለፅ፤ ማንኛውም ሕግን ያልተከተለ ዘረፋ መከላከል ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
በሌላ በኩልም ሪፎርም ባይሠራ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይፈርስ ነበር ብለዋል። ባንኩ ያለበትን ዕዳ በቀላሉ ማኔጅ የሚያደርገው አልነበረም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሪፎርሙ 900 ቢሊዮን ብር የተራዘመ ቦንድ አግኝቷል በከፍተኛ ደረጃ የተጋረጠበትን አደጋ መከላከል የሚያስችል ሃብት አግኝቶ ሥራ ጀምሯል ብለዋል።
ባንኮች ሕግ እና ሥርዓት አክብረው የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገትን በሚያረጋግጥ መንገድ ሊሠሩ ይገባል እንጂ፤ በባንክ ስም የአራጣ ሥራ የሚሠሩ ከሆነ ችግር ነው ብለዋል።
በስም ያልጠቀሷቸው አንዳንድ ኤምባሲዎች የኢትዮጵያን ሃብት በመዝረፍ እና የውጭ ምንዛሪ ቢዝነስ ላይ የተሠማሩ እንዳሉ ጠቁመዋል። እንዲህ አይነት ድርጊት የሚፈጽሙት ላይ ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግና የማይታረሙ ከሆነ እርምጃ እንደሚወሰድ አሳስበዋል። ጤናማ ዝምድና የማያደርግ ማንም ኤምባሲ አንፈልግም ሲሉ ገልጸዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ሦስት ወራት የብሔራዊ ባንክ ተቀማጭ ገንዘብ 161 በመቶ አድጓል። የግል ባንኮች ተቀማጭም 29 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ጠቅሰዋል።
ባለፉት ሦስት ወራት 180 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን፣ ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች የወጪ ንግድ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውቀዋል።
በሩብ ዓመቱ የተገኘውን የወጪ ንግድ ገቢ ማስቀጠል ከተቻለ በዓመት ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስገኘት እንደሚቻልም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከነበረችበት የወጪ ንግድ ገቢ የተሻሻለች ቢሆንም መድረስ ካለባት ግብ አልደረሰችም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ ገቢ በሚቀጥሉት ዓመታት 100 ቢሊዮን ዶላር ማድረስ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ባለፉት ሦስት ወራት ስድስት ነጥብ አራት በመቶ ብልጫ ያለው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ የተቻለው የሀገሪቱ የፋይናንሻል ሥርዓት በመሻሻሉ መሆኑንም ገልጸዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ሰፊ ዕድል አለ። መሬት የሕዝብና የመንግሥት መሆኑ፤ ርካሽና ንጹሕ የኃይል አማራጭ መኖሩና ከዚህ በተጨማሪም በትይዩ ገበያው መካከል ያለው ክፍተት እንዳይሰፋ መሠራቱን በአብነት አንስተዋል።
በሩብ ዓመቱ ለነዳጅ 35 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ድጎማ ተደርጓል፣ በበጀት ዓመቱ 400 ቢሊዮን ዶላር ለድጎማ መመደቡን ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ በሦስት ወራት ለነዳጅ 35 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ድጎማ መደረጉን አስታውቀዋል።
ለነዳጅ የሚደረገው ድጎማ በሚቀጥለው ዓመት 100 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችልም ጠቁመዋል። ድጎማው እጅ አጠር ሰዎች በትራንስፖርት አገልግሎት እንዳይጎዱ ለማድረግ መሆኑን አንስተዋል። ለዘይት ዘጠኝ ቢሊዮን ብር፣ ለሴፍቲኔት 80 ቢሊዮን፣ ለማዳበሪያ 53 ቢሊዮን መመደቡንም ነው የተናገሩት።
ኢትዮ ቴሌኮም ከማገናኘት አልፎ በኢ- ኮሜርስ ከፍተኛውን ድርሻ የሚጫወት ተቋም ሆኗል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢ-ኮሜርስ በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ እንደዋና ሥራው ወስዶ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ከ4ጂ ኔትወርክ ወደ 5ጂ ኔትወርክ ከአዲስ አበባ ወጥቶ በክልል ከተሞች እያስፋፋ መሆኑንም ገልጸዋል።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም