የቲክቶክ ባለቤት ባይትዳንስ መስራች በቻይና ቁጥር አንድ ሀብታም ሆነ

የባይትዳንስ መስራች የሆነው ዛንግ ይሚንግ በ49 ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ቁጥር አንድ የቻይና ባለሀብት መሆኑን ዓመታዊው የሀብታሞች ዝርዝር መረጃ ማሳየቱን ሮይተርስ ዘግቧል።

እንደዘገባው ከሆነ በሪልኢስቴት እና በታዳሽ ኃይል የተሰማሩት አቻዎቹም ከፍተኛ ፉክክር አሳይተዋል።

ከባይትዳንስ ሥራ አስፈጻሚነት በ2021 የለቀቀው የ41 ዓመቱ ዛንግ የሁሩን የቻይና የሀብታሞች ዝርዝር ለመጀመሪያ ጊዜ ከታተመ ወዲህ በ26 ዓመት ውስጥ 18ኛው የቻይና ሀብታም ግለሰብ ለመሆን በቅቷል።

ዛንግ የአንደኛነቱን ቦታ የነጠቀው፣ የሀብት መጠኑ በ24 በመቶ ቀንሶ 47 ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ከሆነበት የታሸገ ውሃ ባለሀብቱ ዞንግ ሻንሻን ነው።

ምንም እንኳን ከቲክቶክ ጋር በተያያዘ አሜሪካ ውስጥ የህግ ክርክር ቢያጋጥመውም፤ የባይትዳንስ ዓለም ዓቀፍ ገቢ ባለፈው ዓመት 30 በመቶ አድጎ 110 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንና ይህም የዛንግ ሀብት መጠን እንዲጨምር እንደረዳው ተገልጿል።

ሶስተኛ ደረጃ የያዘው ብዙም የማይታወቀው የቴንሴንት መሰራች ፖኒ ማ ሲሆን የፒዲዲ ሆልዲንግስ መሰራች የሆነው ኮሊን ሁዋንግ ደግሞ ባለፈው ዓመት ከነበረው የሶስተኛ ደረጃ ዝግ ብሎ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በቻይና የቢሊየነሮች ቁጥር በ142 ቀንሶ 753 ደርሷል። ይህ በ2021 ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ከነበረው ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ከአንድ ሶስተኛ በላይ ቀንሷል ተብሏል።

“ለቻይና ኢኮኖሚ እና ስቶክ ማርኬት ከባድ አመት ነበር” ሲሉ የሁሩን ሪፖርት ሊቀመንበር ሩፔርት ሁግወርፍ ተናግረዋል።

የከፍተኛ የሀብት ቅነሳ የታየው በቻይና ሪልኢስቴት ዘርፍ እንደሆነ የገለጹት ሁግወርፍ፤ የኤሌክትሪክ ፍጆቻ እቃዎች ዋጋ በፍጥነት ማደጉን እና የዣኦሚ መስራች 5 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ገቢ ማግኘቱን ገልጸዋል።

ሁግወርፍ እንዳሉት ከሆነ የሶላር ፖኔል፣ ሊቲየም ባትሪ፣ የኤሌክትሪክ መኪና ሰሪዎች የገበያ ውድድሩ በመጠንከሩ ምክንያት አመቱ ፈታኝ ሆኖባቸው ነበር።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You