“ማህበራዊ ፍትህ” የሚለውን ሀረግ አውዳዊ ፍቺ ስንመለከት፡- ምጣኔ ሀብትን/ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ አቅምን ከምዝበራና ብክነት በመታደግ በአግባቡ ማስተዳደርን ጨምሮ ተጠቃሚ መሆን ለሚገባቸው አካላት ሁሉ የየድርሻቸውን ሀብት በፍትሃዊነት ማከፋፈል መቻል የሚል ትርጉሜ ልንሰጠው እንችላለን::
ማህበራዊ ፍትህን ማስፈን ዛሬም ድረስ በበርካታ ሀገራትና ከተሞች ፈተና የሆነ ችግር ነው:: በአፍሪካ፤ በኢሲያ፤ በመካከለኛና ሩቅ ምስራቅ ሀገራት እንዲሁም በአውሮፓ፤ ዛሬም ድረስ ማህበራዊ ፍትህን የሚጠይቁ ሰልፎች፤ ልዩ ልዩ የአመጽ እና መሰል እንቅስቃሴዎች በስፋት ሲካሄዱ ማየት የተለመደ ነው::
ይህም ሆኖ በዓለም ላይ ያሉ ሀገራት እንደ ጥቅል ስልጣኔያቸው ሀብት የማስተዳደር ሥርዓታቸውና ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው፤ ያላቸውን ሀብት በአግባቡ በማስተዳደርና በመጠቀም እንዲሁም ለዜጎቻቸው በሚገባቸው አግባብ በፍትሃዊነት ማከፋፈል መቻልን ጨምሮ ጥቅል ሀገራዊ ደስተኝነትን ለማረጋገጥ አበክረው ይሰራሉ:: በዚህ ረገድም የተሳካላቸው እና ምሳሌ መሆን የሚችሉ ሀገራት ጥቂቶች የሚባሉ አይደሉም::
በዚህም መነሻነት ማህበራዊ ፍትህን ለማረጋገጥ በየደረጃው የሚደረጉ ትግሎችን በተደራጀ አግባብ ማስኬድ ይቻል ዘንድ፤ በአውሮፓ ሀገራት የበርካቶችን ቅቡልነት አግኝተው ገነው የወጡ በማህበራዊ ፍትህ እና ማህበራዊ ዴሞክራሲ ስም “social justice and social democracy“ የሚታወቁ አውራ የፖለቲካ ርዮተ ዓለማዊ አስተሳሰቦች ከመኖራቸውም ባለፈ፤ ውጤት እያመጡ ስለመሆናቸውም በስፋት ይነገራል::
በኢትዮጵያም በተመሳሳይ መልኩ በ1966 በዘውዳዊው ሥርዓት ላይ ተማሪዎች፤ መምህራን፤ አርሶ አደሮች፤ የታክሲ ሹፌሮችን ጨምሮ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ማህበራዊ ፍትህ በሀገሪቱ እንዲረጋገጥ ያስችላል ያሏቸውን በርካታ ጥያቄዎችን ይዘው አደባባይ በመውጣት መጠየቃቸው በታሪክ የሚታወስ ነው:: በወቅቱ ትውልድ የማህበራዊ ፍትህ አንጓ ሆነው በአብነት ከተወሰዱና ከተጠየቁ ጥያቄዎች መካከል “መሬት ለአራሹና ፤ ትምህርት ለሁሉም” የሚሉት በጉልህ የሚጠቀሱ ናቸው::
በመንግሥታት የለውጥ ሂደት ለዘመናት ማህበራዊ ፍትህንና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን ማረጋገጥ እንዲቻል፤ በሀገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በርዕሰ መዲናዋ አዲስ አበባ ሲከናወኑ የነበሩ የልማት ሥራዎችን በሚፈለገው ፍጥነትና ጊዜ ጀምሮ መጨረስ ብዙ ቢባልበትም አዳጋች የነበረ መሆኑ በስፋት ታይቷል:: አዳዲስ የልማት ሥራዎችን ደረጃ በደረጃ መጀመርን ጨምሮ ቅንጅታዊ የፕሮጀክት አመራር ሥርዓት ውስንነት በጉልህ የታየ ከመሆንም አልፎ በየአካባቢው ለተደጋገመ ጊዜ የብሶት፤ የሕዝባዊ ቁጣና አብዮት ምንጭ የነበረም ነው::
እንደ መንግሥታቱ ጠባይ በየጊዜው ማህበራዊ ፍትህን ማረጋገጥን ጨምሮ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን ማስፈን እንዲቻል ታስበው በሚሰሩ ፕሮጀክቶች ብክነትና ምዝበራን ጨምሮ ሌሎችም በተጓዳኝ የተስተዋሉ በርካታ ችግሮች የነበሩ መሆናቸው ይታወሳል:: እነዚህም በወቅቱ መቅረፍ ያልቻሉ ችግሮች በተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎችና ምሁራን እንዲሁም በሚመለከታቸው አካላት ተደጋጋሚ ወቀሳ የሚሰነዘርባቸው ጉዳዮች ሆነውም ነበር::
በዚህ ረገድ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎችም ወሳኝ ማህበራዊ ፍትህንና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን ለማረጋገጥ እንዲቻል በሚል፤ በየደረጃው በሁሉም ስፍራ ሲሰሩ የነበሩ ሀገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶች የገጠማቸው የፕሮጀክት አመራር ችግርና ምዝበራ በዋቢነት ሊጠቀስ የሚችል ይሆናል::
በተመሳሳይ መልኩ እስከ ወርሃ መጋቢት 2010 ዓ.ም በሀገሪቱ የሥርዓትና የመንግሥት ለውጥ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስም፤ የማህበራዊ ፍትህ መረጋገጥን ጉዳይ አጀንዳ አድርገው የተደራጁ ልዩ ልዩ የፖለቲካ አደረጃጀቶችን ጨምሮ በሚፈለገው ልክና አግባብ ምላሽ ያላገኙ በርካታ ጥያቄዎችም እንደነበሩ አንድ ሁለት እያሉ መነጋገርና መጥቀስ የሚቻል እንጂ ሌላ ውስብስብ መረጃ የሚጠይቀን ጉዳይ አይደለም::
አንደ ሀገር መጪውን ትውልድ ታሳቢ ያደረገ ዘላቂ እድገትን ለማረጋገጥ በትውልድ ቅብብሎሽ ሂደት በሚደረጉ ትግሎች፤ ማህበራዊ ፍትህ እንዲረጋገጥ መሥራትን ጨምሮ የዜጎች ደስተኝነት እውን እንዲሆን በቅንጅት ተባብሮ የድርሻን አስተዋጽኦ ማበርከት ከሁሉም የሚጠበቅ ሀገራዊ ኃላፊነት መሆኑ አያጠያይቅም::
በተጨባጭ ያለን የመንግሥት ሀብት በሚገባ ማስተዳደር በመቻልና ለዜጎች ጥቅም በሚፈለገው አግባብ በማከፋፈል ሂደት የስካንዲኔቪያን ሀገራት በዓለም ላይ ምሳሌ ተደርገው የሚጠቀሱ ናቸው:: በዚህም በዜጎች የደስተኝነት መጠንም በዓለም ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ::
በወርሃ መጋቢት 2010 ዓ.ም በሀገሪቱ የተደረገውን የሥርዓትና የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ ለማህበራዊ ፍትህ መረጋገጥ፤ በርካታ ሰው ተኮር የልማት ተግባራትና ተጓዳኝ የልማት ዕቅዶች ተነድፈውና ተይዘው ተግባራዊ እየተደረጉ ነው። ከዚህ ውስጥ በአዲስ አበባ የሚካሄዱት ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች/የልማት ተጠቃሽ ናቸው::
ከለውጡ ማግስት አንስቶ በሀገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በከተማዋ፤ ምዝበራና ብልሹ አሰራርን ጨምሮ በፕሮጀክት አመራር ወቅት በሀገሪቱ በጉልህ ሲስተዋሉ ከነበሩ ሌሎችም ተጓዳኝ ችግሮች ትምህርት በመውሰድና ፈጣን ማስተካከያ በማድረግ፤ አስቀደመው የነበሩ ጅምር ሥራዎችን ማስቀጠልን ጨምሮ አዳዲስ ሥራዎችን ባጠረ ጊዜ ጀምሮ መጨረስ በከተማዋ ልምድ ሆኗል::
አዲስ አበባ እየተከተለች ባለችው የሰው ተኮር የልማት መርህ በከተማዋ ከ60ና 90 ቀናት ባጠረ ጊዜ፤ በርካታ ማህበራዊ ፍትህንና ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍልን ለማስፈን እንዲቻል የላቀ አስተዋጽኦ የሚኖራቸው የልማት ሥራዎች ባልተለመደ መልኩ ተተግብረዋል:: የልማት ሥራዎቹ በከተማዋ ሁሉም አካባቢዎች በተጨባጭ መታየታቸው ደግሞ እንኳንም ነዋሪዎች በቅን ልቦና የልማት ሥራዎችን አይቶ ለመመስከር የውስጥ ነጻነት ላለው ሰው የተሰወረ አይደለም::
አዲስ አበባ በሀገሪቱ በርካታ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች የሚኖሩባት ግንባር ቀደም ጥንታዊት ከተማ እንደመሆኗ ሁሉ፤ ባለፉት ዓመታት በየደረጃው ከተማ አስተዳደሩ በሰው ተኮር የልማት መርህ ተግባራዊ የሚያደርጋቸው ፕሮጀክቶች እነዚህን ነዋሪዎቿን ታሳቢ ያደረጉ፤ የኑሮ ጫናቸውን ማቃለል ዓላማ ያደረጉ ናቸው::
ለአብነት ያክል በተከታታይ ዓመታት ተገንብተው ለአገልግሎት ብቁ የተደረጉ ወደ 30 ሺ ገደማ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች፤ ከ35 ሺ በላይ በየደረጃው ያሉ ቤቶች እንዲሁም በ2016 በጀት ዓመት ብቻ 7ሺ 567 ቤቶች በከተማ አስተዳደሩ በጀትና ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በሚወጡ ባለሀብቶች ድጋፍ ተገንብተው ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች መስጠት መቻላቸው በከተማዋ የሚከናወኑ የልማት ተግባራት ደሃ ተኮር ስለመሆናቸው ማረጋገጫ ናቸው::
በ2016 በጀት ዓመት ብቻ ከተማዋ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት አስተባብራ ልዩ ልዩ ማህበራዊ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ማዋል መቻሏን ጨምሮ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አቅመ ደካሞችን በመለየት ማዕድ በአውዳ ዓመት ወቅቶች ማጋራት መቻሏም የዚሁ እውነታ ሌላኛው ማሳያ ነው::
በተጠናቀቀው የ2016 የበጀት ዓመት፤ ከ18ሺ 91 በላይ ልዩ ልዩ ለማህበራዊ ፍትህ መረጋገጥ የላቀ አስተዋጽኦ የሚኖራቸው ፕሮጀክቶች ከ60ና 90 ቀናት ባጠረ ጊዜ ተገንብተው ለሕዝባዊ አገልግሎት ክፍት ተደርገዋል:: በበጀት ዓመቱ ለሦስት መቶ ሺህ የከተማዋ ነዋሪዎች ልዩ ልዩ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ከመቻሉም በተጓዳኝ፤ መፍጠር ከተቻለው የሥራ ዕድል መካከልም ሁለት መቶ 91 ሺህ የሚሆነው ቋሚ ናቸው::
ከተማ አስተዳደሩ በተመሳሳይ ማህበራዊ ፍትህና ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍልን የማረጋገጥ አድማሱን በማስፋት 800 መቶ ሺህ ተማሪዎችን በቀን ሁለት ጊዜ መመገብ፣ ዩኒፎርምና የትምህርት ቁሳቁሶችን ማቅረብ፤ እንዲሁም በጥናት በተለዩ አካባቢዎች በተቋቋሙ ሃያ አንዱም የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት በቀን ለአንድ ጊዜ እንኳን ምግብ ማግኘት የሚቸገሩ ዜጎችን በመደገፍ ላይ ነው::
እስከ ዛሬ ከነበረው የበጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም በተቃራኒ ከተማ አስተዳደሩ የ2016 በጀቱን 63 በመቶ ለካፒታል ሥራዎች ማዋል መቻሉን፤ ይህም የተደረገው በሚፈለገው ልክና አግባብ በከተማዋ ማህበራዊ ፍትህን ማረጋገጥ እንዲቻል ታስቦ ነው። ለ2017 በጀት ዓመት ደግሞ በተመሳሳይ ከ230 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት ማጽደቁ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሊታሰብ የሚችል ነው ::
ከዚህም በጀት ላይ 146 ቢሊዮን ብር (63.6%) ካለፈው ዓመት ጋር በተመሳሳይ ለካፒታል ሥራዎች እንዲመደብ የተደረገ ሲሆን፣ 74 ነጥብ 55 ቢሊዮን ብር (33.4%) ለመደበኛ ወይም ለአስተዳደራዊ ወጪዎች እንዲውል መወሰኑንም የምናስታውሰው ነው:: ይህም የተደረገው በከተማዋ በተሟላ መልኩ ማህበራዊ ፍትህን ለማረጋገጥ የሚሰሩ ሥራዎችን በይበልጥ ማስፋት እንዲቻል ታስቦ ነው።
ለካፒታል ከተመደበው ውስጥ 90 ነጥብ 4 በመቶ የሚሆነው ለድህነት ቅነሳ እና ዕድገት ተኮር ዘላቂ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲውል የተመደበ መሆኑ ደግሞ የከተማዋ፤ ማህበራዊ ፍትህን የማረጋገጥ የሰው ተኮር እንቅስቃሴ ቀጣይነት ያለው መሆኑን አጉልቶ የሚያሳይ ነው። አስቀድመን የጠቀስናቸውን ጨምሮ በቅዳሜና እሁድ ገበያ፤ በቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራምና በሌሎችም ከተማ አስተዳደሩ”በሰው ተኮር መርህ” በከተማዋ ማህበራዊ ፍትህን ለማረጋገጥ ለሚያከናውናቸው ተግባራት ልዩ ልዩ ዕውቅናና ሽልማቶች በተለያዩ ጊዜያት ወስዷል::
እነዚህ በየጊዜው ለሕዝባዊ አገልግሎት ክፍት የተደረጉ የልማት ሥራዎች የከተማዋን ጎስቋላ ገፅታ በሚፈለገው አግባብ እየለወጡ ያሉ፤ ማህበራዊ ፍትህንና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ሥርዓትን ያስተዋወቁ፤ ከወትሮ በተሻለ ሰፋፊ የሥራ ዕድሎችን ለከተማዋ ወጣቶች የፈጠሩ፤ ወሳኝ የመንግሥት አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ ያሳለጡ ከመሆናቸውም ባሻገር የከተማዋን ገቢ ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገሩ ናቸው::
በጋዜጠኛና ሲኒየር የኮሙኒኬሽን
ባለሙያ ላንዱዘር አሥራት
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም